ትራምፕ በአሜሪካ የመንግስት ሰራተኞች ላይ በ"ሚም" ሲሳለቁ...
ፕሬዝዳንቱ የካርቱን ምስሉን ያጋሩት ለመንግስት ሰራተኞች በላኩት የኢሜል መልዕክት ተቃውሞው ለበረታባቸው ኤለን መስክ ድጋፋቸውን ለማሳየት ነው ተብሏል

መስክ "ባለፈው ሳምንት ምን አምስት ጉዳዮችን ፈጽማችኋል?" የሚል ጥያቄን የያዘ የኢሜል መልዕክት መስደዳቸው ተቃውሞ አስነስቶባቸዋል
የ78 አመቱ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት የየእለት የመገናኛ ብዙሃን ትኩረት መሆናቸውን ቀጥለዋል።
በትናንትናው እለት ያጋሩት አስቂኝ የካርቱን ምስልም በሌላው አለም ያለውን ፈገግ ቢያሰኝም የሚመለከታቸውን አካላት ግን አስከፍቷል።
"ስፖንጅቦብ" የተሰኘውን የካርቱን ፊልም ገጸባህሪ በመጠቀም የተሰራው "ሚም" በአሜሪካ የፌደራል የመንግስት ሰራተኞች ላይ የሽሙጥ እና ስላቅ መልዕክት የያዘ ነው።
ይህን ምስል ቢሊየነሩ የትራምፕ አጋር ኤለን መስክ በኤክስ ገጻቸው ከለጠፉት በኋላ ፕሬዝዳንቱ በራሳቸው የማህበራዊ ትስስር ገጽ "ትሩዝ ሶሻል" አጋርተውታል።
መስክ የመንግስት ሰራተኞች ባለፈው ሳምንት የሰሯቸውን አምስት ጉዳዮች ዘርዝረው እንዲልኩ የሚጠይቅ የኢሜል መልዕክት ልከዋል። ምላሽ የማይሰጡ ሰራተኞችም በስራ ገበታ ላይ እንደሌሉ ተቆጥሮ ከስራ እንደሚሰናበቱ ማስጠንቀቃቸው ተቃውሞ አስነስቶባቸዋል።
አንዳንድ ተቋማት ሰራተኞቻቸው ለዚህ የኢሜል መልዕክት ምላሽ እንዳይሰጡ ያሳሰቡ ሲሆን፥ በርካቶች በሁኔታው ግራ መጋባታቸውን የአሜሪካ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።
ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ወቀሳ የበዛባቸውን መስክ የሚደግፉ አስተያየቶችን ሲሰጡ መቆይታቸውን ያስታወሰው ኒውዮርክ ፖስት፥ በካርቱን ምስል የተሰራው "ሚም"ም የዚሁ አካል መሆኑን ዘግቧል።
ትራምፕ የመንግስት ሰራተኞች እነዚህን አምስት ምላሾች ሊሰጡ ይችላሉ ሲሉ ተሳልቀዋል።
ምላሾቹ "ስለ ትራምፕ አልቅሻለሁ"፣ "ስለ ኤለን መስክ አንብቻለሁ"፣ "አንድ ጊዜ ስለ ቢሮዬ አልቅሻለሁ"፣ "ስለትራምፕና ኤለን መስክ በድጋሚ አልቅሻለ" እንዲሁም "የተወሰኑ ኢሜሎችን አይቻለሁ" የሚሉ ሊሆኑ ይችላሉ በሚል።
ኤለን መስክም ተመሳሳይ የካርቱን ምስሉን በማጋራት በኢሜል የተላከው ጥያቄ የፌደራል ሰራተኞችን "የልብ ምት የፈተሸ" ነው ብለዋል።
ከ800 ሺህ በላይ አባላትን የያዘው የአሜሪካ የሰራተኞች ማህበር ግን የመንግስት ውጤታማነትን ለማረጋገጥ የተቋቋመውና መስክ የሚመሩት ተቋም የላከውን የኢሜል መልዕክት "ህገወጥ" ብሎታል።
የማህበሩ ፕሬዝዳንት ኤቨርት ኬሊ "ሰራተኞች ለዚህ ህገወጥ የኢሜል መልዕክት ምላሽ ለመስጠት አይገደዱም" ያሉ ሲሆን አቤቱታቸውን ለአሜሪካ የሰው ሃይል አስተዳደር ኤጀንሲ ማስገባታቸውን አብራርተዋል።
ሚኒሶታን የወከሉት የዴሞክራት ሴናተሯ ቲና ስሚዝም ኤለን መስክ አስቸጋሪ አለቃ የሚጠይቀውን ጥያቄ ነው ለፌደራል ሰራተኞች የላኩት ይላሉ። "ቅዳሜ ምሽት የምትመለከቱት የመጥፎ አለቃ የኢሜል መልዕክት አለ፤ ሰኞ ወይም ማክሰኞ እንዲህ እንደምታደርጉ አረጋግጡልኝ አይነት መልዕክት የሚሰድ፤ የኤለን መስክም እንደዛ አይነት ነው፤ እኔ ከቢሊየነሩ አለቃ ሳይሆን ከሰራተኞቹ ወገን ነኝ" ብለዋል።
የአሜሪካ የፌደራል የወንጀል ምርመራ ቢሮ (ኤፍቢአይ)፣ የመከላከያ ሚኒስቴር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሰራተኞች ለመስክ የኢሜል ጥያቄ ምላሽ እንዳይሰጡ ታዘዋል።
ፕሬዝዳንት ዶናልድት ትራምፕ ትናንት ከፈረንሳይ አቻቸው ኢማኑኤል ማክሮን ጋር በዋይትሃውስ መግለጫ ሲሰጡ ለመስክ የኢሜል መልዕክት ምላሽ ያልሰጡ ሰራተኞች ሊባረሩ እንደሚችሉ ተናግረዋል።