የቀድሞቀው ፕሬዝዳንት ኮምፓውሬ በስልጣን ዘመኔ ለፈጸሙት በደል ሁሉ ይቅርታ እንዲደረግላቸው ጠይቀዋል
የቀድሞው የቡርኪና ፋሶ ፕሬዝዳንት ብሌስ ኮምፓውሬ የቶማስ ሳንካራ ቤተሰቦችን ይቅርታ ጠየቁ፡፡
በተቀሰቀሰባቸው ህዝባዊ ተቃውሞ ከስልጣናቸው በመልቀቅ በስደት ይኖሩ የነበሩት ብሌስ ኮምፓውሬ አሁን በስልጣን ላይ ያለው ወታደራዊ መንግስት ባደረገላቸው ምህረት ወደ ኦጋዲጉ ተመልሰዋል፡፡
የቀድሞው ፕሬዝዳንት ወደ ሀገራቸው ከተመለሱ በኋላ በሰጡት መግለጫ “በስልጣን ዘመኔ ቡርኪናቤዎች ላይ ለፈጸምኩት በደል ተጸጽቻለሁ፣ በተለይ የቶማስ ሳንካራ ቤተሰብ ይቅርታ እንዲያደርግልኝ እጠይቃለሁ” ሲሉ ተናግረዋል፡፡
የ71 ዓመቱ የቀድሞው የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት በፈረንጆቹ 2014 ላይ በህዝባዊ አመጽ ከስልጣን የለቀቁ ሲሆን ወደ ጎረቤት ሀገር ኮቲዲቯር ተሰደው ይኖሩ ነበር፡፡
ኮምፓውሬ በሌሉበት ቡርኪናፋሶ ከፈረንሳይ ቅኝግዛት ከወጣች በኋላ የመጀመሪያው ፕሬዝዳንት የነበሩት ቶማስ ሳንካራን ገድለዋል በሚል ክስ ቀርቦባቸው ነበር፡፡
በዚህ ክስ ምክንያትም የእድሜ ልክ እስራት የተፈረደባቸው ብሌስ ኮምፓውሬ ቶማስ ሳንካራን እንዳልገደሉ በተደጋጋሚ ሲናገሩ ቢቆዩም በመጨረሻም ስለ ፈጸሙት በደል ሁሉ ቤተሰባቸው ይቅርታ እንዲያደርግላቸው በይፋ ጠይቀዋል፡፡
የቡርኪናፋሶ የመጀመሪያው ፕሬዘዳንት የነበሩት ቶማስ ሳንካራ ከ34 ዓመት በፊት ነበር የተገደሉት። የሚወዳት ሀገሩን እየመራ የነበረው ቶማስ ሳንካራ አሰቃቂ በተባለ ግድያ ህይወቱ ቢያልፍም በበርካታ አፍሪካውያንና የአፍሪካ ወዳጆች ስሙ ጎልቶ ይነሳል።
በአራት ዓመታት የሥልጣን ዘመኑ ተዓምር የሚያስብሉ ስራዎችን መስራቱንም በርካቶች ይመሰክራሉ።
በአውሮፓውያኑ 1987 በቅርብ ወዳጁ ብሌስ ካምፓውሬ አስተባባሪነት በተመራ መፈንቅለ መንግስት የሳካራ ሕይወትና ስልጣን ተጠናቆ ነበር።
አፍሪካዊው ቼ ጉቬራ እየተባለ የሚጠራው ሳንካራ እንዲገደል አሲረዋል በሚል የተጠረጠሩ 14 ሰዎች ችሎት ቀርበው የሀገሪቱ ፍርድ ቤት በግድያ ወንጀሉ ዙሪያ ከሁለት ወር በፊት ፍርድ መስጠቱ ይታወሳል፡፡
የቶማስ ሳንካራ ባለቤት ከ34 ዓመታት በኋላ የሳንካራ ገዳዮች የፍርድ ሂደትን ስትጠብቀው የነበረ ሁኔታ እንደነበር ገልጻ መንግስት ወደ ሀገራቸው የተመለሱት የቀድሞቀው ፕሬዝዳንት ኮምፓውሬን እንዲያስርላቸውም ጠይቀዋል፡፡