የቡርኪና ፋሶ ፕሬዝዳንት የሀገሪቱን ጠቅላይ ሚኒስትር ከስራ አባረሩ
በቡርኪና ፋሶ ህግ መሰረት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የስራ ከለቀቁ የሀገሪቱ መንግስት እንደሚበተን ይደነግጋል
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከኃላፊነታቸው የተነሱት በሀገሪቱ ያላው የፀጥታ መደፍረስ ምክንያት ነው
የቡርኪና ፋሶ ፕሬዚዳንት ሮክ ማርክ ክርስቲያን ካቦር የሀገሪቱን ጠቅላይ ሚኒስትር ከስራ ማሰናበታቸው ተሰምቷል።
ፕሬዚዳንቱ የቡርኪና ፋሶውን ጠቅላይ ሚኒስትር በትናትናው እለት ከስራ ያሰናበቱ ሲሆን፤ ምክንያታቸው ደግሞ በሀገሪቱ ያላው የፀጥታ መደፍረስ እንደሆነም ተነግሯል።
በሀገሪቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ የመጣው ተቃውሞ ወደ ጎዳናዎች ላይ አመጽ በመቀየር የበረካቶችን ህይወት መቅጠፉ ተነግሯል።
ምዕራብ አፍሪካዊቷ ቡርኪና ፋሶ እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ከ2016 ጀምሮ በተደጋጋሚ የአል ቃይዳ የሽበር ቡድን ጥቃት ሰለባ የሆነች ሲሆን፤ በሽብር ጥቃቶቹም ከ2 ሺህ በላይ መሞታው እና ከ1 ሚሊየን በላይ ሰዎች መፈናቀላቸው ተነግሯል።
ባሳለፍነው ወር ከአል ቃይዳ ጋር ግንኙነት እንዳለው በተነገረ ቡድን በተፈፀመ የሽብር ጥቃት 49 የመከላከያ ፖሊስ አባላት እና 4 ንጹሃን ዜጎች መሞታቸውን ተከትሎ በሀገሪቱ እንደ አዲስ ቁጣ ተቀስቅሷል።
በሀገሪቱ የተቀሰቀሰው ተቃውሞም ፕሬዚዳንት ሮክ ማርክ ክርስቲያን ካቦር ለውጦችን እንዲያደርጉ ጫና እንደፈጠረባቸው ተነግሯል።
ይህንን ተከትሎም ፕሬዚዳንቱ የሀገሪቱ ጦር አመራር ላይ ለውጦችን ማድረጋቸውም ታውቋል።
የቡርኪና ፋሶ ፕሬዚዳንት ጽህፈት ቤትም ፕሬዚዳንት ካቦር ከጠቅላይ ሚኒስትር ክሪስቶፍ ደቢር የስራ መልቀቂያ ደብዳቤ መቀበላቸውን አስታውቋል።
በቡርኪና ፋሶ ህግ መሰረት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የስራ ከለቀቁ የሀገሪቱ መንግስት እንደሚነሳ ይደነግጋል።
ሆኖም ግን አሁን በስራ ላይ ያለው የቡርኪና ፋሶ መንግስት አዲስ መንግስት እስኪመሰረት ድረስ ባለአደራ መንግስት ሆኖ እንደሚቆይም ነው የተገለጸው።
ክሪስቶፍ ደቢር የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው የተሸሙት በአውሮፓውያኑ በ2019 ሲሆን፤ ፕሬዚዳንት ካቦር በድጋሚ መመረጣቸውን ተከትሎም በ2021 ለሁለተኛ ዙር በጠቅላይ ሚኒስትርነት ተሹመው ነበር።