የቀድሞው የኮቲዲቯር ጠቅላይ ሚኒስትር በኮሮና ቫይረስ ተይዘው ህይወታቸው አለፈ
ሟቹ ጠቅላይ ሚኒስትር ኮቲዲቯርን በጠቅላይ ሚኒስትርነት ለሁለት ዓመት መርተው ነበር
የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር በኮሮና ቫይረስ ተይዘው በፓሪስ ህክምና ላይ እያሉ ህይወታቸው አልፏል ተብሏል
የቀድሞው የኮቲዲቯር ጠቅላይ ሚኒስትር በኮሮና ቫይረስ ተይዘው ህይወታቸው አለፈ።
ኮቲዲቯርን ከፈረንጆቹ 2005 እስከ 2007 ዓመት ድረስ በጠቅላይ ሚኒስትርነት የመሩት ቻርልስ ባኒ በኮሮና ቫይረስ ተጠቅተው ሀይወታቸው ማለፉ ተገልጿል።
የወቅቱ የአገሪቱ ፕሬዝዳንት አላሳን ኦታራ በትዊተር ገጻቸው እንዳሉት የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር በ78 ዓመታቸው በህክምና ላይ እያሉ ህይወታቸው አልፏል።
እንደ ፕሬዘዳንቱ መረጃ ከሆነ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ህይወታቸው ያለፈው በኮሮና ቫይረስ ተጠቅተው በፈረንሳይ መዲና ፓሪስ ባለ አንድ ሆስፒታል ህክምና እየተደረገላቸው እያለ ነው።
ሟቹ ጠቅላይ ሚኒስትር በፈረንጆቹ 2010 ዓመት በአገሪቱ ምርጫን ተከትሎ የተፈጠረው እና ከ3 ሺህ በላይ ለሆኑ ዜጎች ህይወት ማለፍ ምክንያት የነበረው ሁከት እና አመጽ እንዲቆም ከፍተኛ ጥረት ካደረጉ ፖለቲከኞች መካከል ዋነኛው ነበሩ።
በተለይም ፖለቲከኞች ወደ ብሄራዊ መግባባት እንዲመጡ፤በህዝብ የተመረጠ ሰላማዊ መንግስት እንዲመሰረት ከፍተኛ ጥረት ማድረጋቸው ይታወሳል።
የኢኮኖሚክስ ምሁር እንደሆኑ የሚነገርላቸው ቻርልስ ባኒ የኮቲዲቯር እና የምዕራብ አፍሪካ አገራት ባንኮች ፕሬዘዳንት በመሆን አገልግለዋል።
ሟቹ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር በፈረንጆቹ 2015 ዓመት በአገሪቱ በተካሄደው ፕሬዘዳንታዊ ምርጫ እጩ የነበሩ ሲሆን በአሁኑ ፕሬዘዳንት አላሳን ኦታራ ሊሸነፉ ችለዋል።