በብራዚል 1 ሺህ 300 ህጻናት በኮቪድ 19 ምክንያት ህይወታቸው አልፏል
በሀገሪቱ በቫይረሱ ሰቢያ ህይወታቸውን የሚያጡ ህጻናት ቁጥር በእጥፍ ሊጨምር እንደሚችል አንድ ጥናት አመልክቷል
በብራዚል እስካሁን በኮቪድ 19 ህይወታቸው ያለፈ ሰዎች ቁጥር 345 ሺህ 287 ደርሷል
የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በዓለማችን ላይ ከተከሰተ ከአንድ ዓመት በላይ ያስቆጠረ ሲሆን፤ በብራዚል በቫይረሱ ምክንያት ህይወታቸውን የሚያጡ ሰዎች ቁጥር ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደርሷል።
ቫይረሱ በሀገሪቱ የአዋቂዎችን ህይወት ብቻ ሳይሆን የህጻናትንም ህይወት እየነጠቀ ስለመሆኑ ከስፍራው የሚወጡ መረጃዎች ያመለክታሉ።
እስካሁንም በሀገሪቱ 1 ሺህ 300 ህጻናት በቫይረሱ ሳቢያ ህይወታቸውን ያጡ ሲሆን፤ ይህም ‘ቫይረሱ በህጻናት ላይ የከፋ ጉዳት አያደርስም’ በሚል የሚነገረውን መረጃ የሚያፋልስ መሆኑን ቢቢሲ በቫይረሱ ህይወቱን ባጣ ህጻን ቤተሰቦች ታሪክ ላይ በሰራው ዘገባ አመላክቷል።
በብራዚል ሳኦ ፖሎ ዩኒቨርሲቲ ኢፒዲሞሎጂስት ዶ/ር ፋቲማ ማሪንሆ “ኮቪድ 19 በህጻናት ላይ የሚያደርሰው አደጋ ዘቅተኛ ነው የሚል የተሳሳተ ግንዛቤ አለ” ይላሉ።
ዶ/ር ፋቲማ ማሪንሆ ባደረጉት ጥናት በብራዚል ብቻ በኮሮና ቫይረስ የተጠቁ ህጻናት ቁጥር አስደንጋጭ በሆነ ሁኔታ ከፍተኛ ሆኖ መገኘቱንም ይናገራሉ።
ከብራዚል የጤና ሚኒስቴር የተገኘ መረጃ እንደሚያመለክተው ከሆነ ካሳለፍነው ዓመት ግንቦት ወር እሰከ ያዝነው ሚያዚያ ወር ብቻ እድሜያቸው እስከ 9 ዓመት የሆኑ 852 ህጻናት፤ እንዲሁም እድሜያቸው ከ1 ዓመት በታች የሆኑ 518 ህጻናት በቫይረሱ ሳቢያ ህይወታቸውን አጥተዋል።
ዶ/ር ፋቲማ ማሪንሆ ግን በሀገሪቱ በቫይረሱ ሰቢያ ህይወታቸውን ያጡ ህጻናት ቁጥር ከዚህ በእጥፍ እንደሚጨምር ባደረጉት ጥናት መለየታቸውን ይናገራሉ።
ለቁጥሩ ማነስ ዋነኛው መንስኤም በምርመራ ወቅት ለህጻናት የሚሰጥ ዝቅተኛ ግምት እና ሪፖርት እንዲሁም የምርመራ አቅም ማነስ እንደሆነም አንስተዋል።
ተመራማሪዎች በበኩላቸው በኮቪድ 19 ምክንያት በህጻናት ላይ የሚከሰተው ሞት አሁንም ዝቅተኛ ነው ሲሉ ይናገራሉ።
ለዚህም በብራዚል ውስጥ በአጠቃላይ በኮቪድ 19 ሳቢያ ከተከሰተው ሞት ውስጥ እድሜያቸው ከ0 እስከ 9 ባሉት ላይ የተከሰተው በመቶኛ ሲለካ 0.58 በመቶ መሆኑንም በማሳያነት ያነሳሉ።
በብራዚል እስካሁን 13 ሚሊየን 673 ሺህ 507 ሰዎች ላይ ኮቪድ 19 ቫይረስ የተገኘ ሲሆን፤ በቫይረሱ ሳቢያ ህይወታቸው ያለፈ ሰዎች ቁጥር 345 ሺህ 287 መድረሱን የሀገሪቱ ጤና ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል።
በሀገሪቱ ያለው የኦክሲጅን መተንፈሻ አቅርቦት እጥረት፣ ለጽኑ ህሙማን የሚያገለግሉ መድሃኒቶች እጥረት እና በሆስፒታሎች ተኝቶ ለመታከም የሚሆን ቦታ ማለቁ ተነግሯል።
ቫይረሱ በሀገሪቱ በዚህ መጠን እየተስፋፋ ቢሆንም የሀገሪቱ ፕሬዝደንት ጃይር ቦልሶናሮ ግን የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት የሚወሰዱ የእንቅስቃሴ ገደብ እና ሌሌች እርምጃመዎች ተፈጻሚ እንዳይሆኑ እንደከለከሉ ነው።