"ምዕራባዊያን በተደጋጋሚ ለአፍሪካ እምነታቸውን አጉድለው እንዴት አብረን እንጓዛለን?"- አቶ ሀይለማርያም
አፍሪካዊያን በምዕራባዊያን ላይ ዕምነታቸው የጠፋው ኔቶ ሊቢያን ከደበደበበት ጊዜ ጀምሮ ነው ብለዋል

አቶ ሀይለማሪያም በሩሲያና ዩክሬን መካከል በሚካሄደው የሀያላን ጦርነ አፍሪካ አቋም እንድትይዝ መጠየቁ ስህተት ነው ብለዋል
በአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ ስር ባለው የሰላምና ደህንነት ኢንስቲትዪት የተዘጋጀው 10ኛው የጣና ፎረም በባህርዳር ተካሂዷል።
ትናንት ፍጻሜውን ያገኘው ይህ ጉባኤ በብዙ የአፍሪካ እና ዓለም አቀፍ የሰላምና ደህንነት ጉዳዮች ዙሪያ ትኩረቱን አድርጓል፡፡
የዚህ ጉባኤ አንዱ አካል የሆነው “የዓለም ደህንነት አለመረጋገጥ በአፍሪካ ላይ ያለው ተጽዕኖ” በሚል ርዕስ ላይ በተካሄደው ውይይት ላይ ከተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት የተውጣጡ የሰላም፣ ፖለቲካ እና ደህንነት ምሁራን፣ መሪዎች እና ሌሎች ተጋባዥ እንግዶች ተሳትፈውበታል።
ይሄንን ውይይት በአውሮፓ ምክር ቤት የውጭ ግንኙነት ክፍል የአፍሪካ ዳይሬክተር የሆኑት ቲዎዶር መርፊ፣ የኦፕን ሶሳይቲ የአፍሪካ ዳይሬክተር፣የዓለም አቀፍ ደህንነት መምህር የሆኑት ካናዳዊቷ ፕሮፌሰር አን ጌራልድ እና ሌሎችም በተወያይነት ተሳትፈውበታል፡፡
በዚህ ውይይት ላይ በአውሮፓ ምክር ቤት የውጭ ግንኙነት ክፍል የአፍሪካ ዳይሬክተር የሆኑት ቲዎዶር መርፊ ከሰባት ወራት በፊት የተጀመረው የሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት አፍሪካን ጨምሮ ሁሉንም አህጉራት እየጎዳ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በዚህ ጦርነት ምክንያት አንዷ ተጎጂ የሆነችው አፍሪካ መሆኗን ያነሱት ዳይሬክተሩ በጦርነቱ ላይ ገለልተኛ መሆን እንደሌለባትም አንስተዋል፡፡
በዚህ ውይይት ላይ ተሳታፊ የሆኑት የኢትዮጵያ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ሀይለማርያም ደሳለኝም በዳይሬክተሩ ለተነሳው ጥያቄ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
አቶ ሀይለማርያም በምላሻቸው ምዕራባዊያን በተደጋጋሚ በአፍሪካ ያላቸውን እምነት ማጣታቸውን ገልጸው፣ ለዓብነትም ከ15 ዓመት በፊት የበለጸጉ ሀገራት ኢንዱስትሪዎች በሚለቁት የተበከለ አየር ምክንያት በታዳጊ ሀገራት ላይ ለሚደርሰው ጉዳት 100 ቢሊዮን ዶላር ለመክፈል የገቡትን ቃል አለማክበራቸውን አንስተዋል፡፡
በሩሲያ እና ዩክሬን መካከል እየተካሄደ ያለው ጦርነት የሀያላኑ ሀገራት ጦርነት ሆኖ ሳለ አፍሪካ አቋም እንድትይዝ መጠየቁ ስህተት መሆኑንም አቶ ሀይለማርያም ደሳለኝ ተናግረዋል፡፡
ምዕራባዊያን በተደጋጋሚ ለአፍሪካ እምነታቸውን አጉድለው እንዴት አብረን እንጓዛለን? አፍሪካዊያን ከምዕራባዊያን ጋር እንዴት እንተባበራለን? ሲሉም ከአወያዮቹ ለቀረበው ሀሳብ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
አቶ ሀይለማርያም አክለውም ምዕራባዊያን በአፍሪካ የነበራቸውን እምነት ያጡት የሰሜን አትላንቲክ ቃል ኪዳን ጦር የአፍሪካ አንድ አካል የሆነችው ሊቢያን በቦምብ ከደበደበ በኋላ ነውም ብለዋል፡፡
የሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነትም የዝሆኖች ጦርነት ነው፣ አፍሪካ በዚህ ጦርነት ላይ አቋም ልትይዝ እንድትይዝ መጠየቁ ትክክል አለመሆኑን በመድረኩ ላይ ተናግረዋል፡፡
አሜሪካ የአፍሪካ ሀገራት ከሩሲያ ጋር ከማዳበሪያ ውጪ ግብይት መፈጸም እንደማይችሉ ያስጠነቀቀች ሲሆን ይሄንን ተላልፎ የሚገኝ ሀገርን እንደምትቀጣ መናገሯ ይታወሳል፡፡
በመንግስታቱ ድርጅት የዋሸንግተን ተወካይ አምባሳደር ሊንዳ ቶማስ በአፍሪካ የነበራቸውን ጉብኝት አጠናቀው ከተመለሱ በኋላ በሰጡት መግለጫ ከሩሲያ ጋር ጥብቅ ግንኙነት ያላቸውን ሀገራት ማስጠንቀቃቸው አይዘነጋም፡፡
የፈረንሳይ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮንም ምዕራብ አፍሪካን በጎበኙበት ወቅት አፍሪካ በሩሲያ ላይ ያሳየችው ለስላሳ አቋም ተገቢ አይደለም ሲሉም ተናግረው ነበር፡፡
ከተመጀረ ስምንት ወራት ሊሞላው ጥቂት ቀናት የቀረው ይህ ጦርነት በየጊዜው አዳዲስ ክስተቶችን በማስተናገድ ላይ ሲሆን አራት የዩክሬን ግዛቶች በህዝበ ውሳኔ ወደ ሩሲያ ሲጠቃለሉ በርካታ ሀገራትም ለዩክሬን የጦር መሳሪያ ድጋፎችን በማድረግ ላይ ናቸው፡፡