ህወሓት የአፍሪካ ህብረትን የተኩስ አቁም ጥሪ እንደሚቀበለው አስታወቀ
መንግስት በአፍሪካ ህብረት ጥላ ስር ለሚደረግ ድርድር ዝግጁ መሆኑ ሲገልጽ ቆይቷል
ህወሓት ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የኤርትራ ጦር ከትግራይ እንዲወጣ ግፊት ያድርግ ሲልም ጠይቋል
ህወሓት በአፍሪካ ህብረት የቀረበውን የአስቸኳይ ተኩስ አቁም ጥሪ እንደሚቀበለው አስታወቀ፡፡
ህወሓት የተክስ አቁም ጥሪውን እንደሚያከበር ያስታወቀው ጦርነት እየተባባሰና በመጣበት እና አፍሪካ ህብረት አፋጣኝ እርቅ እንዲወርድ እየጠየቀ ባለበት ወቅት ነው፡፡
ዳግም ያገረሸውን ጦርነት ተከትሎ በሰሜን ምዕራብ ትግራይ በሽሬ ከተማ በሰላማዊ ሰዎች ላይ ጉዳት መድረሱን አለም አቀፍ ድርጅቶች እየገለጹ ነው፡፡ ተመድ፣ አሜሪካና ሌሎች ምዕራባውያን እየተባባሰ የመጣውን አስከፊ ግጭት ሰላማዊ እልባት እንዲየገኝ ጠይቀዋል፡፡
የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር ሙሳ ፋኪ መሃማት በትናንትናው እለት ባወጡት መግለጫ " መንግስት እና ህወሓት በአፍሪካ ቀንድ ከፍተኛ ተወካይ በሚመራው እና በዓለም አቀፉ መህበረሰብ በሚደገፈው በደቡብ አፍሪካ ወደ ተጠራው የሰላም ድርድር ሊመጡ ይገባል" ሲሉ አሳስበዋል፡፡
ተፋላሚ ኃይሎች ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ የተኩስ አቁም እንዲያደርጉ ያሳሰቡት ሙሳ ፋኪ መሃመት፣ የሰብዓዊ አገልግሎቶች ወደ ነበሩበት አንዲመለሱም ጥሪ አቅርበዋል።
ህወሓት በዓለም አቀፍ ደረጃ ድጋፍ ያገኘ የተኩስ ማቆም ስምምነት እንደሚያከብር ባወጣው መግለጫ አስታውቋል፡፡
“አስቸኳይ የቶክስ አቁም ጥሪ ለማክበር ዝግጁ ነን”ብሏል ህወሓት፡፡
"ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የኤርትራ ጦር ከትግራይ እንዲወጣ፣ ጦርነቱ በአስቸኳይ እንዲቆም ተግባራዊ እርምጃ እንዲወስድ እና የኢትዮጵያ መንግስት ወደ ድርድር ጠረጴዛ እንዲመጣ ግፊት እንዲያደርግ እንጠይቃለን"ም ብሏል፡፡
የኢትዮጵያ መንግስት በጉዳዩ ላይ አስካሁን እስካሁን ያለው ነገር የለም፡፡
ይሁን እንጅ መንግስት በአፍሪካ ህብረት ጥላ ስር በሚካሄድ ድርድር ለመሳተፍ ዝግጁ መሆኑን በተለያዩ ወቅቶች ሲገልጽ መቆየቱ ይታወሳል፡፡
ከሁለት ሳምንታት በፊት በአፍሪካ ህብረት አማካኝነት በደቡብ አፍሪካ ሊካሄድ ታስቦ የነበረው የሰላም ንግግር ላይ የኢትዮጵያ መንግስት እና ህወሓት እንዲሳተፉ ጥሪ አቅርቦ፣ ሁለቱም ወገኖች ተሳታፊ ለመሆን ፈቃደኛ ገልጸው ነበር፡፡
ነገርግን ሊካሄድ የታሰበው ድርድር በሎጂስቲክስ ምክንያት መራዘሙ ይታወሳል፡፡