ሴፕ ብላተር እና ሚሼል ፕላቲኒ በተከሰሱበት የማጭበርበር ሰነድ ችሎት ፊት ቀረቡ
በአንድ ወቅት የዓለም አቀፍ ስፖርት ኃያላን የነበሩ ግለሰቦች እ.ኤ.አ ከ2015 ጀምሮ ከእግር ኳስ መታገዳቸው ይታወሳል
ተከሳሾቹ ጥፋተኛ ሆነው ከተገኙ እስከ አምስት ዓመት የሚደርስ እስራት ሊጠብቃቸው እንደሚችል ተነግሯል
በአንድ ወቅት የዓለም እና የአውሮፓ እግር ኳስ መሪዎች የነበሩት ሴፕ ብላተር እና ሚሼል ፕላቲኒ በተጭበረበረ ክፍያ ተጠርጥረው ችሎት ፊት ቀረቡ፡፡
የስዊዘርላንድ ጠቅላይ አቃቤ ህግ ቢሮ፤ የቀድሞው የፊፋ ፕሬዝደንት ብላተር ለቀድሞው የአውሮፓ እግር ኳስ አስተዳዳሪ ፕላቲኒ የሰጧቸው 1 ነጥብ 6 ሚሊዮን ዩሮ ህገ ወጥ ነው የሚል ክስ አቅርበዋል።
የህግ አዋቂዎቹ ክስ፤ ብላተርን የከሰሰው ያለ አግባብ ገንዘብ በማውጣት እና በወንጀል አያያዝ በሚል ሲሆን፤ በወቅቱ የአውሮፓ እግር ኳስ አስተዳዳሪ የነበሩት ፕላቲኒን ደግሞ እ.ኤ.አ በ2011 ያልተገባ ሁለት ሚሊዮን የስዊስ ፍራንክ (2.08 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር) ተቀብለዋል በሚል ነው፡፡
ይሁን እንጅ እ.ኤ.አ ከ2015 ጀምሮ ሲንከባለል የቆየውን ጉዳይ ብላተር ውድቅ ሲያደርጉት፤ ፕላቲኒ በበኩላቸው የተቀበልኩት ገንዘብ ፊፋን ለማማከር የተከፈለ ነው የሚል መከራከሪያ ሲያቀርቡ መቆየታቸው አይዘነጋም፡፡
በዚህም ሴፕ ብላተር እና ሚሼል ፕላቲኒ በስዊዘርላንድ የፌደራል ወንጀል ችሎት የሁለት ሳምንት የፍርድ ሂደት ባዛሬው እለት መጀመራቸው ኤኤፍፒ ዘግቧል፡፡
የፍርድ ሂደቱ በሰኔ 22 የሚጠናቀቅ ሲሆን ኃምሌ 8 ላይ የመጨረሻው ብይን ይሰጣል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
ተከሳሾቹ ጥፋተኛ ሆነው ከተገኙ እስከ አምስት ዓመት የሚደርስ እስራት ወይም የገንዘብ መቀጮ ሊፈረድባቸው ይችላል ተብለዋል፡፡
በአንድ ወቅት የዓለም አቀፍ ስፖርት ኃያላን የነበሩ ግለሰቦች እ.ኤ.አ ከ2015 ጀምሮ ከእግር ኳስ መታገዳቸው የሚታወስ ነው፡፡