መፈንቅለ መንግስት የተሳተፉ የጊኒ ወታደራዊ አባላት በቀጣይ ምርጫዎች አይሳተፉም ተባለ
ምርጫዎች እንዳይሳተፉም የተባሉት “የጊኒ ጁንታ” አባላት እስከ ምርጫ ድረስ ያለው የሽግግር ጊዜ ላይ ግን ይሳተፋሉ ተብሏል
በጊኒ የሚመሰረተው የሽግግር መንግስት ላይ የሚሳተፉት 81 አባላት መሆናቸው ታውቋል
በጊኒ በሚመሰረተው የሽግግር መንግስት ውስጥ የሚሳተፉ አባላት በሀገሪቱ በቀጣይ በሚደረጉ ብሔራዊ እና ክልላዊ ምርጫዎች ላይ እንደማይሳተፉ ተገለጸ።
በምዕራብ አፍሪካዊቷ ሀገር ጊኒ የተካሄደውንና በሌተናል ኮሎኔል ማማዲ ዱምቦያ የተመራውን መፈንቅለ መንግስት ተከትሎ በሚመሰረተው የሽግግር መንግስት ላይ የሚሳተፉት 81 አባላት መሆናቸው ተገልጿል።
የጊኒ ጁንታ በመባል የሚጠሩትና በመፈንቅለ መንግስት የተሳተፉት ወታደራዊ አባላት በቀጣይ ምርጫዎች እንዳይሳተፉ ቢደረግም እስከ ምርጫ ድረስ ያለው የሽግግር ጊዜ ላይ ግን ስምምነት እንደሚደረግ ተገልጿል።
በጊኒ የተደረገውን መፈንቅለ መንግስት ተከትሎ በቀጣይ በብሔራዊ የሽግግር ምክር ቤት እንደሚመሰረት ሮይተርስ ዘግቧል።
መፈንቅለ መንግስት ያደረጉት የጊኒ ወታደራዊ መሪዎች በሚቋቋመው የሽግግር መንግስት ዙሪያ ሰሞኑን ከታዋቂ ግለሰቦችና ከቢዝነስ ሰዎች ጋር መወያየታቸው ተሰምቷል።
መፈንቅለ መንግስቱን የመሩት ሌተናል ኮሎኔል ማማዲ ዱምቦያ ይቋቋማል ተብሎ የታሰበው የሽግግር መንግስት ፕሬዝዳንት ይሆናሉ ተብሏል።
የሚመሰረተው የሽግግር መንግስት ሲቪል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የካቢኔ አባላት እንደሚኖሩትም ተጠቅሷል፡፡ ከሽግግር መንግስቱ ውስጥ 30 በመቶ የሚሆኑት ሴቶች እንደሚሆኑ ተገልጿል።