“በጊኒ መፈንቅለ መንግስት ከማድረግ ውጭ ምንም አማራጭ አልነበረም”፡-የጊኒ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ዲያሎ
ዲያሎ ጁንታው በሀገሪቱ ሰፍኖ የነበረውን ስርዓት አልበኝነት ያስቀረ በመሆኑ ማዕቀብ ሊጣልበት አይገባም ብሏል
ዲያሎ ፕሬዘዳንት አልፋ ኮንዴ በፈረንጆቹ 2020 ምርጫ አጭበርብረዋል ብለዋል
የጊኒ ተቃዋሚ ቡዱን መሪ ዲያሎ በሀገሪቱ የተደረገውን መፈንቅለ መንግስት ደገፉ፡፡
የቀድሞ የጊኒ ጠቅላይ ሚኒስትርና የተቃዋሚ ቡዱን መሪ ሴሎው ዳሌን ዲያሎ፤ በሀገሪቱ የተካሄደው መፈንቅለ መንግስት በበጎ መልኩ እንደሚመለከቱት አስታውቋል፡፡
ዲያሎ የምዕራብ አፍሪካ መንግስታት የኢኮኖሚ ማህበረሰብ (ኢኮዋስ) በወታደራዊ ጁነታው ላይ የኢኮኖሚ ማዕቀብ እንደይጥልም ተማጽኗል ሲል ኤ.ኤፍ.ፒ ዘግቧል፡፡
"ጁንታው በሀገሪቱ ሰፍኖ የነበረውን ስርዓት አልበኝነት ያስቀረ በመሆኑ ማዕቀብ ሊጣልበት አይገባም" ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትር ሴሎው ዳሌን ዲያሎ፡፡
ለሶስት የምርጫ ዘመናት ያክል ከስልጣን የተወገዱት አልፋ ኮንዴን በፕሬዝዳንታዊ ምርጫ የተፎካከሩት ዲያሎ: “መፈንቅለ መንግስት ከማድረግ ውጭ ምንም አማራጭ አልነበረም”ም ብሏል፡፡
አልፋ ኮንዴን በቁጥጥር ስር በማዋል ካለፈው ቅዳሜ ወዲህ በትረ ስልጣን ጨብጦ የሚገኘውና በሌተናንት ኮሎኔል ማማዲ ደንቦያ የሚመራው ቡዱን ከፍተኛ የሆነ ዲፕሎማሲያዊ ጫና እያስተናገደ መሆኑ ይታወቃል፡፡
በጊኒ መፈንቅለ መንግስት መደረጉን ተከትሎ የምዕራብ አፍሪካ መንግስታት የኢኮኖሚ ማህበረሰብ (ኢኮዋስ) እና አፍሪካ ህብረት ሀገሪቱን ከአባልነት ማገዳቸው የሚታወስ ነው፡፡
ኢኮዋስ ወደ ጊኒ የላከውን የልኡካን ቡዱን ሪፖርት ላይ ተሞርኩዞ ኢኮኖሚያዊ ማዕቀብ ለመጣል ውሰኔ ቢያሳልፍም ዲያሎ ግን ውሳኔው ተገቢ እንዳልሆነ ያነሳሉ፡፡
ዲያሎ "የወታደራዊ ጁንታው ጣልቃ-ገብነት ህገወጥነትንና ተዓማኒነት የሌለው ስልጣን ያስቀረ በመሆኑ ለኔ ተገቢ ውሳኔና ድርጊት ነው" ሲሉም ይሞግታሉ፡፡
ኮንዴ በፈረንጆቹ 2020 ምርጫ አጭበርብረውባኛልም ነው ያሉት ዲያሎ፡፡
የ83ቱ ዓመት አዛውንቱ አልፋ ኮንዴ ባለወፈው ዓመት ያካሄዱንት ምርጫ ተከትሎ ከአክቲቪስቶችና ተቃዋሚዎች በኩል በተሰነዘረባቸው ተቃውሞ በርካቶች ወደ ወህኒ ቤት ማጎራቸው “አምባገነንነታቸው” ያሳየ ድረጊት እንደነበር ይነሳል፡፡
ከቅርብ ወራት ጊዜያት ወዲህ በምዕራብ አፍሪካ እየተስተዋለ ያለው ነገር የዴሞክራሲ አቀንቃኞች ነን በሚሉ አካላት ክፉኛ እየተተቸ እና ትኩረት እየተሰጠው ይገኛል፡፡
አክቲቪስቶች “በምዕራብ አፍሪካ እየተስተዋሉ ያሉ ድርጊቶች ቀጠናው በዴሞክራሲ ያለውን እምነት እየሳሳ መምጣቱንና ለመፈንቅለ መንግስት ትልቅ ቦታ መስጠቱ የሚያመላክት ነው” ብለውታል፡፡
ባለፈው ወርሃ ግንቦት ሌላኛዋ የምዕራብ አፍሪካ ሀገር ማሊ መፈንቅለ መንግስትማስተናገዷ የሚታወስ ነው፡፡
የማሊ የሽግግር ባለሥልጣናት በመጪው የካቲት ምርጫን ለማደራጀት ቃል ቢገቡም አኳሃናቸው አጥጋቢ እንዳልሆነ ኢኮዋስ ከቀናት በፊት አስታወቋል፡፡