የቀድሞው የእስራኤል መከላከያ ሚኒስትር እስራኤልን በጦር ወንጀል እና በዘር ማጽዳት ከሰሱ
ሚኒስትሩ ይህን ማለታቸው ከመንግስት አካላት ከፍተኛ ትችት አስነስቶባቸዋል
የቀድሞው ጀነራል ያአሎን በጠቅላይ ሚኒስትር ኔታንያሁ ካቢኔ ውስጥ ያሉ ወግ አጥባቂዎች ፍልስጤማውያን አባረው የአይሁድ መንደር የማቋቋም ፍላጎት አላቸው ብለዋል
የቀድሞው የእስራኤል መከላከያ ሚኒስትር ሞሼ ያአሎን እስራኤል በጋዛ ሰርጥ የጦር ወንጀል እና የዘር ማጽዳት ወንጀል ፈጽማለች ሲሉ ከሰዋል።
ሚኒስትሩ ይህን ማለታቸው ከመንግስት አካላት ከፍተኛ ትችት አስነስቶባቸዋል።
ቀጥተኛ አቋም ያላቸው የቀድሞው ጀነራል ያአሎን በእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ የቀኝ አክራሪ ካቢኔ ውስጥ ያሉ ወግ አጥባቂዎች ፍልስጤማውያን ከሰሜን ጋዛ አባረው የአይሁድ መንደር የማቋቋም ፍላጎት እንዳላቸው ለእስራኤል ሚዲያዎች ተናግረዋል።
"እየሆነ ስላለው ነገር እና ከእኛ ስለተደበቀው ነገር ለማስጠንቀቅ እገደዳለሁ"ሲሉ ያኣሎን ካን ለተባለው ሚዲያ ባለፈው እሁድ ገልጸዋል።"የጦር ወንጀሎች እየተፈጸሙ ነው።"
ያአሎን በጠቅላይ ሚኒስትር ኔታንያሁ አስተዳደር ስር ከ2013-16 ኢታማዦር ሹም ሆነው የሰሩ ሲሆን ከእዚያን ጊዜ ጀምሮ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ቀንደኛ ተች ናቸው።
የኔታንያሁ ሊኩድ ፓርቲ ያአሎንን "ስም አጥፊ ወሬዎች" በማሰራጨት የከሰሳቸው ሲሆን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ሳአር ደግሞ ያቀረቡት ክስ መሰረተቢስ ነው ሲሉ አጣጥለውታል።
"እስራኤል ሁሉንም ነገር የምትከውነው አለምአቀፍ ህግን ከግምት በማስገባት ነው፤ የቀድሞው ሚኒስትር ያአሎን ያደረሰውን ጉዳት አለመረዳቱ እና ማስተባበያ አለመስጠቱ አሳፋሪ ነው" ብለዋል ውጭ ጉዳይ ሚኒስተሩ።
አለምአቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት (አይሲሲ) ባለፈው ወር ኔታንያሁን እና ከኃላፊነት የተነሱትን መከላከያ ሚኒስትሩን ዮአብ ጋላንትን በጋዛ ጦርነት የጦር ወንጀል እና በሰብዓዊነት ላይ ወንጀል ፈጽመዋል በሚል ጠርጥሮ የመያዣ ትዕዛዝ አውጥቶባቸዋል።
ኔታንያሁ እና ጋላንት የቀረበባቸውን ክስ አይቀበሉትም። ነገርግን ያአሎን ከዲሞክራቶች ቴሌቪዥን ጣቢያ ጋር ባለፈው ቅዳሜ ባደረጉት ቃለ ምልልስ መንግስት"ለማሸነፍ፣ ለመጠቅለል እና የዘር ማጽዳት ለመፈጸም" መሻሉ ሀገሪቱ መስቀለኛ መንገድ ላይ አስቀምጧታል ሲሉ አስጠንቅቀዋል።
ፍልስጤማውያን እስራኤል ከመሬታቸው ልታፈናቅላቸው እንደምትፈልግ በተደጋጋሚ ክስ ሲያሰሙ ቆይተዋል።
በጥቅምት 2023 ሀማስ በእስራኤል ላይ ያደረሰውን ጥቃት ተከትሎ እስራኤል በወሰደችው መጠነሰፊ ጥቃት የተገደሉ ፍልስጤማውያን ቁጥር ከ44ሺ አልፏል።