የቀድሞ የእስራኤል የስለላ ድርጅት ኃላፊ ያጋለጧቸው በጠቅላይ ሚኒስትር ኔታንያሁ የተሰጧቸው ሚስጥራዊ ትእዛዞች
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሀገሪቱን የስለላ እና የመከላከያ ኃላፊዎች በድብቅ ያሰልሉ ነበር ተብሏል

ጽህፈት ቤታቸው ባወጣው መግለጫ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሚስጥራዊ ዘመቻዎችን ደህንነት ለማስጠበቅ በወሰዱት እርምጃ የማንንም መብት አልጣሱም ብሏል
ከ2011 -2016 የእስራኤል የሀገር ውስጥ ደህንነት መስርያቤት ሀላፊ የነበሩት ዮራም ኮኸን ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ በሀገሪቱ ከፍተኛ ባለስልጣናት ላይ የሚያሳልፏቸውን ሚስጥራዊ ትዕዛዞች አጋልጠዋል፡፡
እስራኤል በኢራን የኒውክሌር ማብላያ ጣብያዎች ላይ ጥቃት ለመፈጸም አስባለች ተብሎ በሚነገርበት በዚህ ወቅት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በካቢኔዎቻቸው ላይ እምነት እንዳልነበራቸው የቀድሞ ሀላፊው ተናግረዋል፡፡
የሀገር ውስጥ ደህንነት ሀላፊ የነበሩት ዮራም ኮኸን “ከካን ሬሼት ቤት” ሬዲዮ ጋር በነበራቸው ቆይታ “ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተለይ በደህንነት እና መከላከያ መስርያ ቤት ሀላፊዎች ላይ ጥርጣሬ ነበራቸው፤ በወቅቱ የእስራኤል የመከላከያ ሀይል ዋና አዛዥ እና የሞሳድ ዳይሬክተርን እንድሰልል ጠይቀውኝ ይህን ማድረግ እንደማልችል ነግሪያቸዋለሁ” ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ከኢራን ጥቃት ጋር በተያያዘ በኋላፊዎቹ ላይ ማንኛውንም የስለላ መሳሪያ በሚስጥር ጥቅም ላይ እንዲያውሉ ተጠይቀው እንደነበር የገለጹት የቀድሞ ዳይሬክተር፤ ስለላው ማንም ሰው የጥቃቱን እቅድ ለሚዲያዎች በሚስጥር አሳልፎ የሚሰጥ ከሆነ አስቀድሞ እርምጃ ለመውሰድ እንደሚያስችል ነግረውኛል ነው ያሉት፡፡
ታይምስ ኦፍ እስራኤል እንደዘገበው ከሆነ ኔታንያሁ በወቅቱ የእስራኤል መከላከያ ሃይል (አይዲኤፍ) ሃላፊ ቤኒ ጋንቴዝን እና በወቅቱ የሞሳድ ሃላፊ የነበሩትን ታሚር ፓርዶን ለመከታተል የፈለጉበት ምክንያት ሁለቱም የኢራን የኒውክሌር መርሃ ግብር ላይ ጥቃት ለመሰንዘር ከፍተኛ ሚስጥራዊ እቅዶችን ያውቁ ስለነበር ነው፡፡
የቀድሞ የስለላ ሊቅ አክለውም የጥቅምት 7ቱ የሀማስ ጥቃት በመከላከያው ድክመት የተፈጠረ እንደሆነ ለማስመሰል የኔታንያሁ አስተዳደር ሰፊ የሚድያ ዘመቻ ሲያደርግ እንደነበር መታዘባቸውን ተናግረዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ኔታንያሁ የቀረበባቸውን ውንጀላ ተከትሎ በሰጡት ምላሽ “ኮኸን ትልቅ የስልጣን እና የፖለቲካ ፍላጎት ያለው ሰው ነው፤ ይህን ህልሙን ለመሳካት ሌላ ተጨማሪ ውሽትን የማይዋሽበት ምክንያት የለም” ሲሉ አስተባብለዋል፡፡
በተጨማሪም ጽህፈት ቤታቸው ባወጣው መግለጫ “ጠቅላይ ሚኒስትሩ አንድን ወሳኝ የመንግስት ሚስጥር ለመጠበቅ የህግ አማካሪዎቻቸውን ሀሳብ በመከተል፣ በህጉ መሰረት እርምጃ ወስደዋል፤ በዚህም የማንንም መብት አልጣሱም” ብሏል።
የቀድሞ የመከላከያ ሃላፊ ቤኒ ጋንቴዝ ከኮኸን ቃለ መጠይቅ በኋላ በሰጡት ምላሽ “በኔታንያሁ ድርጊት አልተገረምኩም፤ ምክንያቱም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሁል ጊዜ አካባቢያቸው ላይ ላሉ ሰዎች መርዛማ እና አጠራጣሪ አመለካከት አላቸው” ነው ያሉት።
የቀድሞ የመከላከያ ሀላፊ የአሁኑ የናሽናል ዩኒቲ ፓርቲ መሪ ጋንቴዝ አክለውም “የበሰሉ አሰራር እቅዶችን ወደ እርሱ ይዤ ስመጣ ሁሌም በጥርጣሬ ይመለከተኝ ነበር፤ ከእቅዱ ጀርባ የተደበቀ ነገር ይኖር ይሆን በሚልም ለማጣራት ሙከራ ያደርጋል” ብለዋል፡፡
በእስራኤል ታሪክ ለረጅም ጊዜ በስልጣን ላይ በመቆየት የመጀመርያው መሪ የሆኑት ኔታንያሁ ከ2009 -2021 ድጋሚ ደግሞ ከ2022 ጀምሮ እስራኤልን እያስተዳደሩ ይገኛሉ፡፡