
በአሜሪካ የሚደገፉ የሶሪያ ኩርድ ታጣቂዎችም ዴል ኤል ዞር የተሰኘችውን ከተማ መያዛቸው በአሳድ መንግስት ላይ ጫናውን አበርትቶታል
የሶሪያ አማጺያን በአንድ ሳምንት ውስጥ አራት ከተሞችን ተቆጣጠሩ።
አማጺያኑ ከ13 አመት በፊት በፕሬዝዳንት በሽር አል አሳድ ላይ ህዝባዊ አመጽ ሲቀሰቀስ መነሻ የነበረችውን ደራ ከተማ በዛሬው እለት መያዛቸውን አስታውቀዋል።
ከአልቃይዳ ጋር ግንኙነት ያለው "ሃያት ታህሪር አል ሻም" የተሰኘውና ሌሎች አማጺ ቡድኖች በኢድሊብ ግዛት ካለፈው ሳምንት ጀምሮ መጠነሰፊ ማጥቃት ጀምረዋል።
ከደማስቆ በ100 ኪሎሜትር ላይ የምትገኘው ከተማ በአማጺያኑ መያዝ በፕሬዝዳንት በሽር አል አሳድ ጦር እና በደጋፊዎቹ ላይ ጫና እንደሚፈጥር ሬውተርስ ዘግቧል።
በማህበራዊ ሚዲያዎች የወጡ ምስሎች የከተማዋ ነዋሪዎች በደስታ አደባባይ መውጣታቸውን ቢያሳዩም የሶሪያ መንግስት እስካሁን ማረጋገጫ አልሰጠም።
ከ13 አመት በፊት የእርስ በርስ ጦርነት ከመጀመሩ በፊት 100 ሺህ ነዋሪዎች የነበሯት ደራ ከአሌፖ፣ ሀማ እና ሆምስ በመቀጠል በአማጺያኑ ቁጥጥር ስር የገባች ከተማ ሆናለች።
በአሜሪካ የሚደገፉ የሶሪያ ኩርድ ታጣቂዎች ዴል ኤል ዞር የተሰኘችውን ከተማ መያዛቸውን አስታውቀዋል።
በ2017 በአሜሪካ መራሹ ጦር የተሸነፈው አይኤስም በምስራቃዊ ሶሪያ የተወሰኑ አካባቢዎችን መቆጣጠሩ መገለጹ የበሽር አል አሳድ መንግስት ጦር ላይ ስጋቱ እንዲያይል አድርጓል።
የሶሪያ መንግስት ቴሌቪዥን ሩሲያ እና ሶሪያ በሀማ፣ ኢድሊብ እና አሌፖ በአማጽያኑ ላይ በፈጸሙት የአየር ድብደባ በጥቂቱ 200 ሰርጎገቦች መገደላቸውን ዘግቧል።
በኢራን የሚደገፉ የሄዝቦላህ ሃይሎች በሆምስ ከተማ ዙሪያ የሶሪያ መንግስትን እየደገፉ መሆኑ ቢገለጽም ሄዝቦላህ ማረጋገጫ ከመስጠት ተቆጥቧል።
ሶሪያ ከቱርክ ጋር የምትዋሰንባት አሌፖ፤ ከዮርዳኖስ ጋር ድንበር የምትጋራባት ደራ በአሜሪካ፣ ሩሲያ እና ቱርክ በሽብር በተፈረጀው ሃያት ታህሪር አል ሻም መያዛቸውና ሌሎች አማጺ ቡድኖችም እንቅስቃሴያቸውን ማጠናከራቸው የአሳድ ደጋፊ ሀገራት አስቸኳይ ምክክር እንዲጠሩ አድርጓል።
የሶሪያውን ፕሬዝዳንት የሚደግፉት ኢራን እና ሩሲያ በሶሪያ ተቃዋሚዎችን ከምትደግፈው ቱርክ ጋር ዛሬ በኳታር መዲና ዶሃ እንደሚወያዩ ተገልጿል።