በዓለማችን ታዋቂዋ የባሕር ወፍ “ዊዝደም” በ74 አመቷ እንቁላል መጣሏ መነጋገርያ ሆኗል
በ1956 ጀምሮ በተመራማሪዎች ክትትል ሲደረግባት የቆየችው አዛውንቷ ወፍ በእድሜ ማምሻዋ ላይ እንቁላል መጣሏ አዲስ ነገር ነው ተብሏል

የዚህ ወፍ ዝርያ አማካይ የእድሜ ጣራ 45 አመት መሆኑን ተከትሎ 70 አመታትን የመዘልቋ ሁኔታ ምርምር እየተካሄደበት ይገኛል
'ዊዝደም' ወይም ጥበብ በሚል መጠርያ የተሰየመችው የዓለማችን ታዋቂዋ ወፍ በ74 አመቷ እንቁላል መጣሏ በእንስሳት ሕይወት ተመራማሪዎች ዘንድ መነጋገርያ ሆኗል፡፡
“አልባትሮሰስ” የተሰኘው የባሕር የወፍ ዝርያ በየአመቱ ህዳር ወር “ሚድዌ አቶል” ወደተባለው ደሴት በመምጣት ከወንድ ወፎች ጋር ጥምረት ይፈጽማሉ፡፡
የዚህ ዝርያ አካል የሆነችው “ዊዝደም” በፓስፊክ ውቅያኖስ በሚገኘው በዚህ ደሴት ለመጀመርያ ጊዜ የታየችው በ1956 ሲሆን፤ ከዚህ ጊዜ ጀምሮ ተመራማሪዎች የረጅም ጊዜ የምርታማነት ምልክት እንደሆነች በመቁጠር ሲከታተሏት ቆይተዋል፡፡
“የአልባትሮሰስ” የወፍ ዝርያዎች እንቁላል መጣል የሚጀምሩት ከአምስት አመታቸው ጀምሮ መሆኑን ተከትሎ “ዊዝደም” አሁን ላይ እንቁላል የጣለችበት እድሜ 74 እንደሚሆን ተመራማሪዎቹ ተናግረዋል፡፡
በአጠቃላይ የምድር ቆይታዋ እስካሁን ከ50-60 እንቁላሎችን እንደጣለች የሚነገርላት ወፍ ከዚህ ውስጥ 30 የሚሆኑት በተሳካ ሁኔታ ተፈልፍለው ማደጋቸው ነው የተገለጸው፡፡
የስነህይወት ተመራማሪዋ ዶክተር ቤት ፍሊንት “ዊዝደም በየአመቱ ወደ ደሴቱ በምትመለስበት ጊዜ የባሕር ወፎች ረጅም ዕድሜ የመኖርና የመራባት ችሎታን የበለጠ እንድናጠና እና እንድንማር አግዞናል” ብለዋል።
እስካሁን በሕይወት መቆየቷ የወፍ ወዳዶች እና ተመራማሪዎች እነዚህን ወፎች እና መኖሪያዎቻቸውን ይበልጥ መጠበቅ ብንችል ተፈጥሮን ለረጅም ጊዜ ማቆየት እንደምንችል ያየንበት ነው ሲሉ አክለዋል፡፡
ተመሳሳይ ዝርያዎች አይደለም በ70ዎቹ እድሜ ውስጥ እንቁላል ለመጣል አማካይ የእድሜ ጣራቸው ከ45 አመት በላይ እንደማይሻገር ተገልጿል፡፡
“የአልባትሮስስ” የባህር ወፎች እንቁላል የመፈልፈያ ጊዜ ከ64-65 ቀን የሚወስድ ሲሆን በደሴቱ የሚጣሉ የወፍ እንቁላላሎች እስከ 80 በመቶ ድረስ የመፈልፈል እድል አላቸው፡፡