ጃፓን 37 ሚሊየን ዜጎቿ መብራት እንዲያጠፉ አሳሰበች
በጃፓን የሙቀን መጠን እየጨመረ መምጣቱን ተከትሎ የኃይል መቆራረጥ ሊያጋጥም እንደሚችል ተሰግቷል
ቶኪዮን ጨምሮ በስምንት አከባቢዎች የኤሌክትሪክ ኃይል የማመንጨት አቅም በ3.7 በመቶ ይቀንሳል ተብሏል
የጃፓን መንግስት በሀገሪቱ በተከሰተው ከፍተኛ ሙቀት ሳቢያ የኃል አቅርቦት እጥረት እንዳይከሰት በቶኪዮና አካባቢው ያሉ ሰዎች የኤሌክትሪክ ፍጆታቸውን እንዲቀንሱ አሳስቧል።
የጃፓን የኢኮኖሚ፣ ንግድ እና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር እንዳስታወቀው በዛሬ እለት ከከሰዓት ጀመሮ በሀገሪቱ ያለው የኃይል ፍላጎት ከፍተኛ ሊሆን እንደሚችል አስታውቋል።
ስለዚህም በቶኪዮና አካባቢው ያሉ ሰዎች አላስፈላጊ መብራቶችን ማጥፋት አለባቸው ያለው ሚኒስቴሩ፤ የሙቀት መጨመርን ለማስወገድ የአየር ማቀዝቀዣን መጠቀም እንዳለባቸውም አሳስቧል።
በጃፓን የሙቀን መጠን እየጨመረ መምጣቱን ተከትሎ የሀገሪቱ ባለስልጣናት የኃይል መቆራረጥ ሊያጋጥም እንደሚችል ለሳምንታት ሲያስጠነቅቁ ሰንብተዋል።
ሚኒስቴሩ እንዳስታወቀው ዛሬ ከሰዓት በኋላ በቶኪዮና ስምንት አከባቢዎች የኤሌክትሪክ ኃይል የማመንጨት አቅም በ3.7 በመቶ ይቀንሳል ተብሎ ይጠበቃል።
በዚህም የሚያጋጥመውን የሃይል እጥረት ለመቋቋም የጃፓን ዜጎች ዛሬ ከሰዓት ከ9 ሰዓት በኋ ለ3 ሰዓታት ያክል መብራቶችን እንዲያጠፉ ያሳሰበ ሲሆን፤ በአንጻሩ የአየር ማቀዝቀዣዎችን አንዲጠቀም አስታውቋል።
ጃፓን ከሰሞኑ በከፍተኛ ሙቀት የተመታች ሲሆን፤ በሳምንቱ መጨረሻ፣ በማዕከላዊ ቶኪዮ ያለው የሙቀት መጠን ከ35 ዲግሪ ሴንትግሬድ በላይ ከፍ ብሏል።
እንዲሁም ከዋና ከተማው በስተሰሜን ምዕራብ የምትገኘው ኢሴሳኪ ከተማ ደግሞ 40.2 ዲግሪ ሴንትግሬድ ሆኖ ተመዝግቧል፤ ይህም በሰኔ ወር ለጃፓን ከተመዘገበው ከፍተኛው የሙቀት መጠን ነው።