ሩሲያ የጃፓን ጠቅላይ ሚኒስትር ወደ ሀገሯ እንዳይገቡ አገደች
ሩሲያ እገዳውን ያስተላለፈችው ጃፓን ከሌሎች ምዕራባዊያን ሀገራት ጋር ማበሯን ተከትሎ ነው
እገዳው ከፉሚዮ ኪሺዳ በተጨማሪ በሌሎች የጃፓኑ ባለስልጣናት ላይ የተጣለም ነው
ሩሲያ የጃፓን ጠቅላይ ሚኒስትር ወደ ሀገሯ እንዳይገቡ አገደች፡፡
ሩሲያ የጃፓን ጠቅላይ ሚኒስትር ፉሚዮ ኪሺዳን ወደ ሀገሯ እንዳይገቡ እገዳ መጣሏን ገልጻለች፡፡
ከጠቅላይ ሚኒስትር ኪሺዳ በተጨማሪም በርካታ የጃፓን ባለስልጣናት ወደ ሞስኮ መግባት እንዳይችሉ ማዕቀብ ተጥሎባቸዋል ሲል ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
ሩሲያ በጃፓን ከፍተኛ ባለስልጣናት ላይ እቀባውን ያስተላለፈችው አሜሪካ እና የአውሮፓ ህብረትን ጨምሮ በሩሲያ ላይ ከ6 ሺህ በላይ የተለያዩ ማዕቀቦችን ማስተላለፋቸውን ተከትሎ ነው፡፡
ዩክሬን የሰሜን አትላንቲክ ቃልኪዳን ጦርን እቀላቀላለሁ ማለቷን ተከትሎ ሩሲያ በኪቭ ልዩ ዘመቻ በሚል ይፋዊ ጦርነት መጀመሯ ይታወሳል፡፡
ሩሲያ ጎረቤቷ ዩክሬን ኔቶን እቀላቀላለሁ ማለቷን ተከትሎ ከፈረንጆች የካቲት 24፤ 2022 ጀምሮ ወታደራዊ ዘመቻ ማካሄድ መጀመሯ ይታወቃል።
በየሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት ምክንያት ከ6 ሚሊዮን በላይ ዜጎች ሀገራቸውን ለቀው ወደ ጎረቤት ሀገራት ለመሰደድ እንደተሰደዱም ዓለም አቀፉ የፍልሰተኞች ድርጅት ያወጣው ሪፖርት ያመለክታል።
ሩሲያ በዩክሬን ላይ እየወሰደች ያለውን ወታደራዊ እርምጃ ከጅምሩም ቢሆን የተቃወሙት ምዕራባውያን፤ ሩሲያን ያዳክማሉ ያሉዋቸው ማዕቀቦች ሲጥሉ እየተስተዋሉ ነው።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት(ተመድ) ጠቅላላ ጉባኤ ባደረገው ስብሰባ ሩሲያ ዩክሬንን መዉረሯን የሚያወግዘዉን የዉሳኔ ሀሳብ በአብላጫ ድምጽ ማጸደቁም እንዲሁ የሚታወስ ነው።
የተመድ ጠቅላላ ጉባኤም ሩሲያ ተመድ የሰብአዊ መብት ምክርቤት በአብላጫ ድምጽ እንድትታገድ ያደረገ ሲሆን ሩሲያም ይህን ተከትሎ ከም/ቤቱ አባልነት መውጣቷን ማስታወቋ ይታወሳል፡፡