የቀድሞው የጃፓን ጠቅላይ ሚንስትር ሺንዞ አቤን የቀብር ስነ ስርዓት ተፈጸመ
በቀብር ስነ ስርዓቱ ላይ የአሜሪካ ምክትል ፕሬዝዳንት ካማላ ሃሪስን ጨምሮ የተለያዩ ሀገራት መሪዎች ተገኝተዋል
የቀብር ስነ ስርዓቱ ቢያንስ 12 ሚሊዮን ዩሮ ገደማ ወጪ ማስወጣቱ አነጋጋሪ ሆኗል
ጃፓናውያን የቀድሞ የጃፓን ጠቅላይ ሚንስትር ሺንዞ አቤ ብሄራዊ የቀብር ስነ ስርዓት አከናውነዋል።
በብሄራዊ የቀብር ስነ ስርዓቱ ላይ የሟች ባለቤት አኪ አቤን ጨምሮ በሺዎች የሚቆጠሩ ሃዘንተኞች በቶክዮ መገኘታቸው መገናኛ ብዙሃን በመዘገብ ላይ ናቸው፡፡
የአሜሪካ ምክትል ፕሬዝዳንት ካማላ ሃሪስ፣ የሲንጋፖር ጠቅላይ ሚኒስትር ሊ ህሲየን፣ የህንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ እንዲሁም የአውስትራሊያው ጠቅላይ ሚኒስትር አንቶኒ አልባኔዝ ከቀድሞ የሀገራቸው ሶስት መሪዎች ጋር በስነ-ስርዓቱ መገኘታቸውንም ኤኤፍፒ ዘግቧል፡፡
በቀብር ስነ-ስርዓቱ ላይ ንግግር ያሰሙት የጃፓን ጠቅላይ ሚኒስትር ፉሚዮ ኪሺዳ፤ ሺንዞ አቤን “በሕገ መንግስታዊ ታሪካችን ለረጅም ጊዘያት በስልጣን የቆዩ፤ ነገር ግን ታሪክ ከቆይታ ጊዜያቸው ይልቅ ባስመዘገቡት ስኬት የሚያስታውሳቸው መሪ” ሲሉ ያላቸውን ክብር ገልጸዋል፡፡
በሌላ በኩል በጃፓን ለንጉሳውያን ቤተሰቦች ብቻ የሚደረገው ብሄራዊ የቀብር ስነ ስርዓት ቢያንስ 12 ሚሊዮን ዩሮ ገደማ ወጪ ማስወጣቱ አነጋገሪ ሆኗል፡፡
በዚህም የተነሳ በሺዎች የሚቆጠሩ የጃፓን ግብር ከፋዮች ተጋነነ ያሉትን ወጪ ለመቃወም በቶክዮ ጎዳናዎች ላይ የተቃውሞ ሰልፍ ሲያደርጉ ተስተውለዋል።
መረጃች እንደሚጠቁሙት ከሆነ 57 በመቶ የሚሆኑት ጃፓናውያን የቀብር ስነ ስርዓት ሲቃወሙ፣ 32 በመቶው ደግሞ ደግፈውታል፡፡
የቀድሞው የሃገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ሺንዞ አቤ ከሁለት ወራት በፊት ለፓርቲያቸው በመቀስቀስ ላይ ሳሉ በሰሜን ምዕራባዊ የሃገሪቱ ክፍል ናራ ከተማ ጎዳና ላይ መገደላቸው ይታወሳል።
በገጠማቸው የጤና እክል ምክንያት በፈቃዳቸው ስልጣን የለቀቁት አቤ ጃፓንን ለሁለት ያህል ጊዜያት በጠቅላይ ሚኒስትርነት አገልግለዋል።
ስልጣን ለመጀመሪያ ጊዜ ሲይዙ በዕድሜ ትንሹ የሃገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ነበሩ።
አቤኖሚክስ በሚል ምጣኔ ሃብታዊ ፍልስፍናቸው ሃገራቸውን ግዙፍ ምጣኔ ሃብትን ከገነቡ ሃገራት ተርታ ለማሰለፍ ችለው የነበረም ሲሆን ጃፓን በተሻለ የዲፕሎማሲ እመርታ ላይ እንድትደርስ ስለማስቻላቸውም ይነገራል።
አቤ ህገ መንግስታዊ ማሻሻያ በማድረግ የሃገራቸውን ጦር የማጠናከር ውጥናቸውን ሳይፈጽሙ ነው የተገደሉት።
ሆኖም ተተኪያቸው ኪሺዳ የሺንዞ አቤን ውጥኖች ከዳር ለማድረስ እንደሚሰሩ ቃል መግባታቸው የታወቃል፡፡