የቀድሞው የማንችስተር እግር ኳስ ክለብ ተጫዋች የሀገር ፕሬዝዳንታዊ ምርጫን አሸነፈ
ገለሰቡ ከእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ በተጨማሪም በስዊዝ ሊግ ተጫውቶ አሳልፏል
ተመራጭ ፕሬዝዳንቱ ከሁለት ሳምንት በኋላ ስልጣን ይረከባል
የቀድሞው የማንችስተር እግር ኳስ ክለብ የሀገር ፕሬዝዳንታዊ ምርጫን አሸነፈ።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ስፖርተኞች ወደ ፖለቲካው እየተቀላቀሉ ሲሆን የቀድሞው ኤሲሚላን እና ፒኤስጂ እግር ኳስ ክለብ ተጫዋች የነበረው ጆርጅ ዊሀ የላይቤሪያ ፕሬዝዳንት ሆኖ ማገልገሉ ይታወሳል።
አሁን ደግሞ የቀድሞ የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ተጫዋች የነበረው ሚካኤል ካቬላስቪል የጆርጅያ ፕሬዝዳንት ሆኖ ተመርጧል።
የ53 ዓመቱ የቀድሞው ተጫዋች ለማንችስተር ሲቲ እግር ኳስ ክለብ 28 ጊዜ ተሰልፎ ሶስት ጎሎችን አስቆጥሯል።
ተመራጩ ፕሬዝዳንት ከእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ባለፈ ለስዊዝ ክለቦችም ተጫውቷል።
እንዲሁም ለሀገሩ ጆርጂያ ብሔራዊ ቡድን ተሰልፎ 10 ጎሎችን ያስቆጠረ ሲሆን ከፈረንጆቹ 2016 ጀምሮም የሀገሪቱ ህግ አውጪ ምክር ቤት አባል ነበር።
ዛሬ በተካሄደ ምርጫም የሀገሪቱ ህግ አውጪ ምክር ቤት አባላት በአብላጫ ድምጽ የጆርጂያ ፕሬዝዳንት እንዲሆን ተመርጧል።
ከ15 ቀናት በኋላም በይፋ ቃለ መሀላ ፈጽሞ ስራ እንደሚጀምር የተገለጸ ሲሆን በስልጣን ላይ ያሉት ፕሬዝዳንት ሳሎሜ ዛሩቢችቪሊ በሀላፊነቴ እቀጥላለሁ ብለዋል።
በስልጣን ላይ ያሉት ፕሬዝዳንት ለተመራጩ ፕሬዝዳንት ስልጣን አላስረክብም ያሉት ምርጫውን ያካሄደው ምክር ቤት ህጋዊ አይደለም በሚል ነው።
ተመራጩ ፕሬዝዳንት ከአውሮፓ ህብረት ይልቅ ለሩሲያ የቀረቡ ናቸው የተባሉ ሲሆን ስልጣን አላስረክብም ያሉት ተሰናባቹ ፕሬዝዳንት ደግሞ አፍቃሬ ብራስልስ ናቸው ሲል ዩሮ ኒውስ ዘግቧል።