ጠቅላይ ሚኒስትር ኢምራን መንግስታቸውን ለመገልበጥ የተሸረበው ሴራ መክሸፉን ገልጸዋል
የፓኪስታን ፕሬዝዳንት በጠቅላይ ሚኒስትር ኢምራን ካሃን ጥያቄ የሃገሪቱን ፓርላማ በተኑ፡፡
የፓርላማው መበተን በቶሎ ምርጫ ለማድረግ በማሰብ የተደረገ ነው ተብሏል፡፡
የኢምራን ካሃን መንግስት ተቃዋሚ የፓርላማ አባላት ህግ አውጭው የሃገሪቱ ምክር ቤት በጠቅላይ ሚኒስትሩ ላይ መተማመኛ ድምጽ እንዲሰጥ ጠይቀው ነበር፡፡
ተቃዋሚዎቹ የቀድሞው የክሪኬት ኮኮብ ከስልጣን ለማስወገድ ከ342ቱ የምክር ቤቱ አባላት የ172ቱን ድጋፍ ማግኘት ብቻ ነበር የሚጠበቅባቸው፡፡
የጠቅላይ ሚኒስትሩ ፓርቲ አጣማሪ ሆኖ ወደ ምክር ቤቱ የገባው ፓርቲ የተቃዋሚዎቹን ጥያቄ መደገፉም ለጥያቄው አቅራቢዎች የልብ ልብ የሰጠ ነበር፡፡
ሆኖም የምክር ቤቱ ምክትል አፈ ጉባዔ ጥያቄው የአገዛዝ ለውጥ ለማድረግ በማሰብ የቀረበ ነው በሚል ወድቅ አድርገውታል፡፡
ይህ ሲሆን ከሰሞኑ በሩሲያ ጉብኝት ላይ የነበሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ኢምራን ካሃን በፓርላማው አልነበሩም፡፡ ሆኖም በሃገሪቱ ብሔራዊ ቴሌቪዥን ቀርበው ፕሬዝዳንት አሪፍ አልቪ ምክር ቤቱን እንዲበትኑ እንደሚጠይቁ ተናግረው ነበር፡፡
መንግስታቸውን ለመገልበጥ የተሸረበው ሴራ መክሸፉን በማሳወቅም ፓኪስታናውያን ለምርጫ እንዲዘጋጁም ካሃን ጠይቀዋል፡፡
ተቃዋሚዎቼ ሊገለብጡኝ ከአሜሪካ ጋር እያሴሩ ነው የሚለውን የጠቅላይ ሚኒስትሩን ጥያቄ የተቀበሉት ፕሬዝዳንት አሪፍም ትናንት እሁድ ምክር ቤቱ መበተኑን አሳውቀዋል፡፡
የፓኪስታኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ኢምራን ክሃን “እኛ የምዕራባዊያን ባሪያዎች አይደለንም” አሉ
የፓኪስታን ህገ መንግስት እንዲህ ዐይነት ሁኔታዎች ሲያጋጥሙ በ90 ቀናት ውስጥ ምርጫ እንዲደረግ እስከዚያው ሃገሪቱ በጊዜያዊ የሽግግር መንግስት እንድትመራ ያዛል፡፡ በጊዜያዊ የሽግግር መንግስቱ ተቃዋሚዎች ይካተታሉ፡፡
የምክትል አፈጉባዔውን እርምጃ ክህደት ሲሉ ያወገዙት ተቃዋሚዎች ጉዳዩን ወደ ህግ እንደሚወስዱት ገልጸዋል፡፡
ጉዳዩ እንደቀረበለት ያሳወቀው የሃገሪቱ ጠቅላይ ፍርድ ቤትም ዛሬ ሰኞ አቤቱታዎችን እንደሚያደምጥና ውሳኔውን እንደሚያጤን ትናንት እሁድ አመሻሽ በሰጠው መግለጫ አስታውቋል፡፡
ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ በፕሬዚዳንቱ እና በጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚሰጡ የትኞቹም ውሳኔዎች በህግ አግባብ እንደሚፈጸሙም ገልጿል፡፡
ከሰሞኑ ኑሮ ውድነትን ሰበብ ባደረጉ ተቃውሞዎች ስትናጥ የከረመችው ፓኪስታን ይበልጥ እንዳትበጠበጥ በሚል ጥብቅ የጸጥታና ደህንነት ቁጥጥሮች እየተደረጉ መሆኑን የሃገሪቱ ብዙሃን መገናኛዎች ዘግበዋል፡፡