በሀገሪቱ በነበረው ተቃውሞ ፕሬዝዳንት ጎታባያ ራጃፖክስ ከስልጣን መውረዳቸው ይታወሳል
የስሪላንካ ፓርላማ የቀድሞውን ጠቅላይ ሚኒስትር የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ሆነው መሾማቸውን መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል፡፡
ምክር ቤቱ የቀድሞውን ጠቅላይ ሚኒስትር ራኒል ዊክሬሜሲንጌ የስሪላንካ ፕሬዝዳንት እንዲሆኑ መርጧል። አዲሱ ፕሬዝዳንት ተቀናቃያቸውን 134 ለ 82 በሆነ ድምጽ አሸንፈው ነው ወደ ቤተመንግስት እንዲገቡ የተወሰነላቸው ተብሏል፡፡
ምንም እንኳን ራኒል ዊክሬሜሲንጌ በሀገሪቱ ም/ቤት አዲስ ፕሬዝዳንት ሆነው ቢሰየሙም የህዝብ ተቀባይነት እንደሌላቸው ግን እየተገለጸ ነው፡፡
በስሪላንካ አዲስ መሪ ለማግኘት የተካሄደው ምርጫም ጊዜያዊ ፕሬዝዳንቱንና የቀድሞውን ጠቅላይ ሚኒስትር ሙሉ ስልጣን ሰጥቷል፡፡ ምክር ቤቱ የኮበለሉትን የስሪላንዳ ፕሬዝዳንት የሚተካ መሪ ለማግኘት ያደረገው ምርጫም ተጠናቋል፡ ፡
የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትርና የአሁኑ ጊዜያዊ ፕሬዝዳንት ራኒል ዊክሬሜሲንጌ የፕሬዝዳንታዊ ምርጫው ዕጩ ሆነው መቅረባቸው ቀደም ብሎም የተገለጸ ቢሆንም የተቀባይነታቸው ጉዳይ ግን አሁንም መነጋገሪያ መሆኑ ተጠቅሷል፡፡
አዲሱ ፕሬዝዳንት በውጭ ምንዛሬ እጥረት እየተናጠች ያለችውንና የኢኮኖሚ ድቀት ያንገላታትን ሀገር የመታደግ ብሔራዊ ኃላፊነት ተጥሎባቸዋል ተብሏል፡፡
የሀገሪቱ ታቃዋሚ ፓርቲ መሪ ሳጅዝ ፕሬማዳሳ ከዚህ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ራሳቸውን ማግለላቸው የሚታወስ ሲሆን አሁን ግን ራኒል ዊክሬሜሲንጌ ስደተኛውን የቀድሞው የስሪላንካ ፕሬዝዳንት ተክለው ሰልፈኞች ከሰሞኑ ተቆጣጥረውት ወደነበረው ቤተ መንግስት ሊገቡ ነው፡፡
ስደተኛው የስሪላንካ ፕሬዝዳንት በቅድሚያ ወደ ማልዴቪስ ከዛም ወደ ሲንጋፖር ማቅናታቸው ይታወሳል፡፡
በሀገሪቱ በነበረው ተቃውሞ ፕሬዝዳንት ጎታባያ ራጃፖክስ ከስልጣን ወርደው ወደ ሌላ ሀገር ተሰደዋል።