ባለፈው ሳምንት ብቻ በሊቢያ የባህር ዳርቻ ወደ 1 ሺህ የሚጠጉ ህገወጥ ስደተኞች ከሞት ታድጌያለሁ- አይ.ኦ.ኤም
በአንድ አመት ብቻ በድምሩ “32 ሺህ 425 ህገወጥ ስደተኞች” በቁጥጥር ስር ውሏል
ሊቢያ የሜዲትራንያን ባህርን አቋርጠው ወደ አውሮፓ ለመሻገር ለሚፈልጉ ስደተኞች ተመራጭ የመነሻ ሀገር ናት
ባለፈው ሳምንት ወደ 1 ሺህ የሚጠጉ ህገወጥ ስደተኞች በሊቢያ የባህር ዳርቻ ተይዘው ወደ ሊቢያ እንደተመለሱ የዓለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት (አይ.ኦ.ኤም) አስታወቀ።
አይ.ኦ.ኤም፡ "ከታህሳስ 19 እስከ 25 ባለው ጊዜ ውስጥ 969 ስደተኞች ታድነው ወደ ሊቢያ ተመልሷል" ማለቱንም ሲጂቲኤን ዘግቧል፡፡
በአንድ አመት ብቻ በድምሩ 32 ሺህ 425 ህገወጥ ስደተኞች በቁጥጥር ስር መዋላቸው፣573 ሰዎች መሞታቸው እንዲሁም 933 ስደተኞች ከሊቢያ ባህር ዳርቻ በማእከላዊ ሜዲትራኒያን መንገድ መጥፋታቸው ድርጅቱ ገልጿል።
እንደፈረንጆቹ በ2011 ሟቹ መሪ ሙአመር ጋዳፊ ከወደቁ በኋላ ሀገሪቱ ከነበረችበት አለመረጋጋት እና የፀጥታ ሁኔታ አንፃር፤በርካታ አፍሪካውያን ስደተኞች ሜዲትራኒያን ባህርን አቋርጠው ወደ አውሮፓ የባህር ዳርቻዎች ለመዝለቅ ሊቢያን ሲመርጡ ይስተዋላል።
ይህም የሰሜን አፍሪካዊቷን ሀገር የሜዲትራንያን ባህርን አቋርጠው ወደ አውሮፓ የባህር ዳርቻ ለመሻገር ለሚፈልጉ ስደተኞች ተመራጭ የመነሻ ቦታ አድርጓታል።