ኤርትራን ጨምሮ አራት የአፍሪካ ሃገራት እስካሁን ዜጎቻቸውን መከተብ አልጀመሩም
ኢትዮጵያን ጨምሮ አምስት አገራት በአንጻራዊነት ብዙ ዜጎቻቸውን መከተባቸውም ነው የተነገረው
የኮሮና ክትባቶችን ያገኙ አፍሪካውያን ቁጥር ከአጠቃላይ የአህጉሪቱ ህዝብ ቁጥር ከ1 በመቶ በታች መሆኑ ተገልጿል
የአፍሪካ በሽታ መከላከል እና መቆጣጠር ማዕከል (ሲዲሲ) እንዳስታወቀው ኤርትራ፣ ታንዛኒያ ቻድ እና ቡሩንዲ እስካሁን ድረስ የኮሮና ቫይረስ ክትባቶችን ለዜጎቻቸው መስጠት አልጀመሩም።
አገራቱ በርካታ ዜጎቻቸውን በዚሁ ቫይረስ ምክንያት ቢያጡም እስካሁን ክትባቱን ለዜጎቻቸው መስጠት አልጀመሩም እንደ ማዕከሉ ገለጻ።
በአፍሪካ አስካሁን ባለው የኮሮና ቫይረስ ክትባት ዘመቻ 38 ነጥብ 1 ሚሊዮን አፍሪካዊያን ክትባቱን እንደወሰዱ ተገልጿል።
ሞሮኮ፣ ግብጽ፣ ናይጀሪያ፣ ኢትዮጵያ እና ዚምባብዌ በአንጻራዊነት የተሻለ የኮሮና ቫይረስ ከትባት የሰጡ አገራት እንደሆኑ ማዕከሉ አስታውቋል።
አፍሪካ 53 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዶዝ ክትባት ያስፈልጋታል ያለው ማዕከሉ እስካሁን ክትባቱን ያገኙ አፍሪካዊያን ቁጥር ከአጠቃላይ የአህጉሪቱ ህዝብ ቁጥር ከ1 በመቶ በታች እንደሆነ በድረገጹ አስታውቋል።
ኢትዮጵያ ከ1 ነጥብ 8 ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑ ዜጎቿ የኮሮና ቫይረስ ከትባት መስጠቷን ዶ/ር ሊያ ታደሰ በዕለታዊ ሪፖርታቸው ገልጸዋል።
በአፍሪካ አስካሁን ድረስ 4 ነጥብ 9 ሚሊዮን ዜጎች በኮሮና ቫይረስ የተጠቁ ሲሆን 131 ሺህ 441 ዜጎች ደግሞ ህይወታቸውን እንዳጡ ከማዕከሉ ያገኘነው መረጃ ይጠቁማል።