የኮሮና ክትባቶችን ለሌላው ዓለም ሳታጋራ የቆየችው አሜሪካ 80 ሚሊዬን ክትባቶችን ልትለግስ ነው
ክትባቱን ከሚያገኙ ሃገራት መካከል ግብጽ ትገኝበታለች ተብሏል
ኢትዮጵያ በኮቫክስ የግዢ ስርዓት ብትታቀፍም ክትባቶቹን ስለማግኘት አለማግኘቷ የታወቀ ነገር የለም
የኮሮና ክትባቶችን ለተቀረው ዓለም ላለማጋራት ወስና የቆየችው አሜሪካ ለተለያዩ ሃገራት የ80 ሚሊዬን (ዶዝ) ክትባቶች ድጋፍ ልታደርግ ነው፡፡
ድጋፉ የተለያዩ የደቡብ አሜሪካ እና እስያ ሃገራትን ጨምሮ በኮቫክስ ግዢ ስርዓት ለታቀፉ የአፍሪካ ሃገራት የሚደረግ ነው፡፡
እስከተያዘው ወር (ሰኔ) መጨረሻ ወደየሃገራቱ ይደርሳልም ተብሏል፡፡
25 ሚሊዬን ያህል ክትባቶችን ፈጥና እንደምትለግስም ነው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ትናንት የተናገሩት፡፡
የፋይዘር፣ የሞደርና እና የጃንሰን ናቸው የተባለላቸው ክትባቶቹ ከሃገሪቱ የፌዴራል የክትባቶች ክምችት ፈጥነው እንደሚሰራጩም ተገልጿል፡፡
ሌሎች ተጨማሪ 60 ሚሊዬን የአስትራ ዜኔካ ክትባቶችን ለተቀረው ዓለም እንደምትለግስም ነው አሜሪካ ያስታወቀችው፡፡
ዋሽንግተን ካላት የክትባቶች ክምችት ውስጥ ሩብ ያህሉን ለመጠባበቂያ እና ለአጋሮቿ ይሆን ዘንድ መክተቷም ነው አሶሼትድ ፕሬስ ባለስልጣናትን ዋቢ አድርጎ የዘገበው፡፡
ከመጀመሪያዎቹ 19 ሚሊዬን ክትባቶች መካከል 6 ሚሊዬን ያህሉ ወደ ደቡብ እና መካከለኛው አሜሪካ፣ 7 ሚሊዮኑ ወደ እስያ እና 5 ሚሊዮኑ ደግሞ ወደ አፍሪካ ይላካል፡፡
ቀሪው 6 ሚሊዬን ደግሞ ግብጽን ለመሳሰሉ አጋሮቿ የሚሰጥ ነው፡፡
አሜሪካ ለኮቫክስ የክትባቶች ግዢ ስርዓት የ4 ቢሊዬን ዶላር ድጋፍ አድርጋለች፡፡ ሆኖም ድጋፉ በስርዓቱ የታቀፉ ሃገራትን አልታደገም፡፡
የሃብታም ሃገራት ክትባቶችን ከልክ በላይ ማጋበስና አልጠግብ ባይነት እስካሁን ዜጎቻቸውን ያልከተቡ ሃገራት እንዲኖሩ፤ ብዙዎች ክትባቱን ሳያገኙ እንዲሞቱም ምክንያት ሆኗል፡፡
ኢትዮጵያ በኮቫክስ የግዢ ስርዓት መታቀፏ ይታወቃል፤ ሆኖም የአሜሪካን ክትባቶች ታግኝ አታግኝ የታወቀ ነገር የለም፡፡
በትግራይ ጉዳይ በተለያዩ የኢትዮጵያ ባለስልጣናት ላይ የጉዞ እገዳን የጣለችው አሜሪካ ሰብዓዊ እና ሌሎችንም ድጋች እንደማታቆም ማስታወቋ የሚታወስ ነው፡፡