የምርጫ ቦርድ ውሳኔ በፍ/ቤት መሻሩን ተከትሎ የሐረሪ ብሄረሰብ አባላት በአዲስ አበባ ድምጽ ሰጥተዋል
አብላጫ ድምጽ ያገኘው ብልጽግና ፓርቲ መስከረም 24 መንግስት ይመሰርታል
ምርጫ ቦርድ የሐረሪ ብሄረሰብ አባላት ከክልሉ ውጭ ሆነው በሐረሪ ክልል ለሚወዳደሩ ፓርቲዎች ድምጽ መስጠት አይችሉም የሚል ውሳኔ አሳልፎ ነበር
ምርጫ ቦርድ የሐረሪ ማህበረሰቦች ባሉበት ሆነው በሐረሪ ክልል ላሉ ፓርቲዎች ድምጽ መስጠት አይችሉም የሚል ውሳኔ ማሳለፉን ተከትሎ እና ከዚህ ጉዳይ ጋር በተያያዘ ጉዳዩ ወደ ፍርድ ቤት በማምራቱ ነበር።
ይሁንና የምርጫ ቦርድ ውሳኔ በፍርድ ቤት በመሻሩ ምክንያት የሐረሪ ማህበረሰብ አባላት እንደከዚህ ቀደሞቹ በሚኖሩባቸው አካባቢ ሆነው በመምረጥ ላይ ይገኛሉ። በውሳኔ መሰረትም የብሄረሰቡ አባላት ዛሬ በአዲስ አበባ ድምጻቸውን ሰጥተዋል፡፡
በዚህም መሰረት 14 አባላት ለሚኖሩት የሐረሪ ብሔራዊ ጉባኤ ከሐረሪ ክልል ውጪ የሚኖሩ የሐረሪ ብሔረሰብ አባላት አዲስ አበባን ጨምሮ በአዳማ፤በጅግጅጋ፤በድሬዳዋ እና በምስራቅ ኦሮሚያ ባሉ 12 የምርጫ ጣቢያዎች ድምጽ በመስጠት ላይ ይገኛል።
አል ዐይን አማርኛ በአዲስ አበባ ባሉ የተወሰኑ ምርጫ ጣቢያዎች ተዘዋውሮ የድምጽ አሰጣጡን ሂደት ተመልክቷል።
1 ሺህ 149 መራጮች ካርድ በወሰዱበት በመካኒሳ ምርጫ ጣቢያ በአካል ተገኝተን እንደታዘብነው መራጮች ድምጻቸውን በመስጠት ላይ ይገኛሉ።
ከመራጮች፤ከፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮች ፤ከምርጫ አስፈጻሚ እና ሌሎች ታዛቢዎች ጋር ባደረግነው ቆይታ በእስካሁኑ የምርጫው ሂደት ያጋጠመ ችግር የለም።
ብልጽግና፤ነጻነት እና እኩልነት ፓርቲ እንዲሁም የሐረሪ ዲሞክራሲያዊ ድርጅት በዚህ ምርጫ ላይ እጩዎቻቸውን አቅርበው በመወዳደር ላይ መሆናቸውን ታዝበናል።
በአጠቃላይ በአዲስ አበባ ባሉ ስድስት ምርጫ ጣቢያዎች ከ5 ሺህ በላይ መራጮች እንደተመዘገቡም ሰምተናል።ለቡ፤ፒያሳ፤መካኒሳ፤ቦሌ፤ለገሀር እና መርካቶ አካባቢዎች ለሚኖሩ የሐረሪ ብሔረሰብ አባላት የመርጫ ጣቢያዎች የተቋቋሙባቸው አካባቢዎች ናቸው።
የሐረሪ ብሔራዊ ክልላዊ ምክር ቤት 36 መቀመጫዎች ያሉት ሲሆን ከዚህ ወስጥ 14ቱ መቀመጫዎች የሐረሪ ብሔራዊ ጉባኤ አባላት ናቸው።
በዘንድሮው ጠቅላላ ምርጫ፤ ብልጽግና ፓርቲ አብላጫ ድምጽ ማግኘቱንና ሌሎች ሶስት ተቀዋሚ ፖርቲዎች የፓርላ መቀመጫ ማሸነፋቸውን ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ማስታወቁ ይታወሳል።
ጠቅላላ ምርጫው በተለያየ ምክንያት በሁሉም የምርጫ ክልሎች መካሄድ ባይችልም፣ ምርጫ ቦርድ መንግስት ለመመስረት የሚያስችል ድምጽ መገኘቱን ይፋ አድርጎ ነበር። የህዝብ ተወካዮች ም/ቤትም መስከረም 24 አዲስ መንግስት እንደሚመሰረት ማስታወቁ ይታወሳል፡፡