ዝርፊያ መበራከቱን ተከትሎ በአዲስ አበባ ሞተር ሳይክሎች ከአሽከርካሪዎች ውጭ ሌላ ተሳፋሪ መጫን አይችሉም ተባለ
የአዲስ አበባ ከተማ ትራንስፖርት ቢሮ አዲስ የሞተር ሳይክል ፈቃድና ቁጥጥር መመሪያ ማውጣቱን አስታውቋል
እገዳው ካሳለፍነው ታህሳስ 22 ቀን 2014 ዓ.ም ጀምሮ ላልተወሰነ ጊዜ የሚቀጥል ነው ተብሏል
በአዲስ አበባ ሞተር ሳይክሎች ከአሽከርካሪዎች ውጭ ሌላ ተሳፋሪ እንዳይጭኑ ታገዱ፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የትራንስፖርት ቢሮ የሞተር ሳይክል አሽከርካሪዎች ከአሽከርካሪዎች ውጭ ሌላ ተሳፋሪ እንዳይጭኑ እገዳ ጥሏል፡፡
ቢሮው ለአል ዐይን በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው በከተማዋ በሞተር ሳይክል ምክንያት የሚደርሱ የትራፊክ አደጋዎችንና ህገ ወጥ ድርጊቶችን መከላከል የሚያስችል የሞተር ሳይክል ፈቃድና ቁጥጥር መመሪያ አውጥቻለሁ ብሏል።
በአሁኑ ወቅት ውጭ ሀገር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን፣ ትውልደ ኢትዮጵያውያን እና የኢትዮጵያ ወዳጆች ወደ ሀገር ቤት እንዲገቡ የቀረበውን ጥሪ ተከትሎ በርካታ የዲያስፖራ አባላት ወደሀገራቸው እየገቡ ይገኛል፡፡
በተያያዘ ወቅቱ የበዓል ሰሞን እንደመሆኑ በርካታ የከተማዋ ነዋሪዎች ከቦታ ቦታ በብዛት እንቅስቃሴ እያደረጉ ሲሆን፥ ይህን ተከትሎ በከተማዋ የትራፊክ መጨናነቅ እና የዝርፊያ ምልክቶች እየታዩ መሆኑን ቢሮው አክሏል፡፡
በመሆኑም ከታህሳስ 22 ቀን 2014 ዓ.ም ጀምሮ ላልተወሰነ ጊዜ የሞተር ሳይክል አሽከርካሪዎች ከአሽከርካሪዎች ውጭ ሌላ ተሳፋሪ እንዳይጭኑ ቁጥጥር እንዲደረግ እና እርምጃ እንዲወሰድ ቢሮው መወሰኑን አስታውቋል፡፡