ከአራት ሚሊዮን በላይ ዩክሬናውያን ኤሌክትሪክ አልባ መሆናቸውን ፕሬዝዳንት ዘለንስኪ ተናገሩ
ፑቲን ለኬርች ድልድይ መውደም አጸፋዊ ምላሽ እስጣለው ባሉት መሰረት መጠነ ሰፊ ጥቃት እየሰነዘሩ ነው
ፕሬዝዳንት ዘለንስኪ፤ “ሩሲያ በእኛ ላይ የምትሰነዝረው ጥቃት እኛን አይሰብረንም!” ሲሊ ተደምጠዋል
ሩሲያ በመሰረት ልማቶች ላይ ባደረሰችው ጥቃት ምክንያት ከአራት ሚሊዮን በላይ ዩክሬናውያን ኤሌክትሪክ አልባ መሆናቸው የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዘለንስኪ ገለጹ፡፡
ፕሬዝዳንት ቮሎድሚር ዘለንስኪ ትናንት ምሽት ባደረጉት ንግግር "አራት ሚሊዮን የሚጠጋ ሕዝብ ለችግር የተዳረገ ቢሆንም ይህ ጥቃት ግን እኛን አይሰብረንም!” ሲሊ ተደምጠዋል፡፡
ፕሬዝዳንት ዘለንሰኪ ሩሲያ ኢራን ሰራሽ ሰው አልባ አውሮፕላኖችን በመጠቀም በመላ የዩክሬን ከተሞች ላይ በሰነዘረችው የሀገሪቱ ሶስተኛ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ጣቢያ መውደሙም ተናግረዋል፡፡
ባለቤትነቱ የግል የሆነው የኃይል ኩባንያ ድቴክም ኪቭ ግዛት 30 በመቶ የሚሆነው የኃይል ምንጯን ማጣቷን ገልጸዋል።በዚህም ምክንያት ያልተጠበቀ የኃይል መቋረጥ ማጋጠሙ አይቀሬ ነው ብለዋል።
የኩባንያው ዳይሬክተር ዲሚይትሮ ሳክሃሩክ የደረሰው ጉዳት መጠነ ሰፊ መሆኑንም ተናግረዋል።
የኃይል መቋረጡ በአባወራዎች ከፈጠረው ችግር ባሻገር የመንገድ መብራቶች እና በኤሌክትሪክ የሚሰሩ የህዝብ መጓጓዣ አገልግሎቶች የገደበ ነው ተብሏል፡፡
ይሁን እንጅ በመሰረተ ልማቶች ላይ የሚሰነዘረው ጥቃት አያንበረክከንም የሚሉት ፕሬዝዳንት ዘለንሲኪ፤ በጭለማ የተዋጡት ከተሞች የአሌክትሪክ አገልግሎት እንዲያገኙ ጥረትበመደረግ ላይ መሆኑ አስታውቀዋል፡፡
የሩሲያው ፕሬዝዳንት ፑቲን ከሳምንታት በፊት ከክሬሚያ ጋር የሚያገኛነውን የኬርች ድልድይ ላይ ለደረሰው የቦምብ ጥቃት አጸፋዊ ምላሽ ለመስጠት በዛቱት መሰረት በዩክሬን ላይ መጠነ ሰፊ ጥቃት እየሰነዘሩ እንደሆነ ይታወቃል፡፡
በዚህም ሩሲያ በሰነዘረችው ጥቃት በሳምንት ውስጥ 30 በመቶ የዩክሬን የኃይል ማመንጫ ጣቢያዎችን መውደማቸው የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዘለንስኪ ከቀናት በፊት መግለጻቸውም የሚታወስ ነው፡፡
ፕሬዝዳንቱ፤ የኢነርጂ መሰረተ ልማትን ተደጋጋሚ ኢላማ ያደረገውን የሩሲያ እርምጃ “የሽብር ጥቃት” ሲሉም ሲሉ ገልጸውታል፡፡
"ከጥቅምት 10 ጀምሮ 30 በመቶው የዩክሬን የኃይል ማመንጫ ጣቢያዎች ወድመዋል፤ ይህም በመላ ሀገሪቱ ከፍተኛ የኃል መቆራረጥ እንዲፈጠር አድርጓል" ሲሉም ተናግረዋል ዘለንስኪ ከቀናት በፊት በትዊትር ገጻቸው ላይ ባሰፈሩት መልዕክት።
ጥቃቱ “ከፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን አገዛዝ ጋር ለመደራደር የሚስችል ምንም እድል የለም” እንደማለት ነውም ብለዋል።
ወታደራዊ ተንታኞች በበኩላቸው የወቅቱ የክሬምሊን ባለስልጣናት እርምጃ ሞስኮ በጦር ሜዳ ላይ ለደረሰው ኪሳራ የሰጠችውን ምላሽ ይመስላል ሲሉ ገልጸውታል።
የአሁን ተከታታይ የሰው አልባ አውሮፕላን ሚሳዔሎች ድብደባ የጦርነቱ መጀመሪያ አከባቢ ሞስኮ ኪቭን ለመቆጣጠር ታደርገው የነበረ መጠነ ሰፊ ጥቃት አይነት መሆኑም እተነገረ ነው፡፡