የስፔን ፖሊስ በብራዚላዊው የእግርኳስ ኮከብ ላይ መስርቶት የነበረውን ክስ አቋረጠ
ኔማር ጥፋተኛ ሆኖ ቢገኝ የ10 ሚሊየን ዩሮ እና ሁለት አመት እስራት ይጠብቀው ነበር
ኔይማር ከሳንቶስ ወደ ባርሴሎና ስዘዋወር በነበረው ድርድር ላይ መሳተፌን አላስታውስም ብሏል
እንደፈረንጆቹ በ2013 ብራዘላዊው የእግር ኳስ ኮከብ ኔይማር ጁኒየር ከሳንቶስ ወደ ባርሴሎና ሲዘዋወር በነበርው ሂደት ሙስና ተፈጽሟል በሚል በቅርቡ በስፔን ችሎት ቀርቦ ነበር፡፡
ይሁን እንጅ ባልተጠበቀ ሁኔታ የስፔን አቃቤ ህግ በኔይማር እና ሌሎች ሰዎች ላይ የቀረበውን ክስ አቋርጠዋል፡፡
"በሁሉም ተከሳሾች (ኔይማር ፣ ወላጆቹ እና ጉዳዮቹን የሚመራው የአን አንድ ኤን ኩባንያ) ላይ የቀረበው ክስ ተቋርጧል"ም ነው ያለው አቃቤ ህጉ፡፡
የ30 አመቱ ኔይማር ከብራዚሉ ክለብ ሳንቶስ ወደ ስፔናዊው ቡድን ስዘዋወወር በነበረው ድርድር ላይ መሳተፌን አላስታውስም ሲል መናገሩም ኤኤፍፒ ዘግቧል።
የስፔን አቃቤ ህግ በሚቀጥለው ወር ወደ ኳታር የዓለም ዋንጫ የሚያቀናው የብራዚል ቡድን ቁልፍ አባል የሆነውን ኔይማር ሙስና እና ማጭበርበር ፈጽሟል በሚል የ10 ሚሊየን ዩሮ (9.7 ሚሊዮን ዶላር) ቅጣት እንዲከፍል የሁለት አመት እስራት እንዲቀጣ ጠይቆ እንደነበር አይዘነጋም፡፡
ይሁን እንጅ የአሁኑ ክስ የማቋረጥ ውሳኔ በብራዚላዊው የእግር ኳስ ጠቢብ ላይ ለአመታት የዘለቀው የህግ ሂደት የሚቋጭና ለኔማርም ቢሆን እፎይታ የሚሰጥ ነው ተብሏል፡፡
ኔይማር ጁኒየር እንደፈረንጆቹ በ2017 የዓለም ሪከርድ በሆነ የ222-ሚሊዮን ዩሮ ዝውውር ባለቤትነቱ የኳታር የሆነውን ፓሪስ ሴንት ዠርሜን መቀላቀሉንና ከቡድኑ ጋር የተለየዩ ስኬቶች በማስመዝገብ ላይ መሆኑ ይታወቃል፡፡