ሳምንታዊ የስራ ቀናትን ወደ አራት ቀናት የማውረዱ እቅድ በብዙ ሀገራት ተቀባይነት እያገኘ ነው ተባለ
በርካታ የአውሮፓ ሀገራት የአራት ስራ ቀናትን ለመተግበር የጀመሩት የሙከራ ጊዜ ስኬታማ ሆኖ እንዳገኙት ተገልጿል
በቤልጂየም ከሁለት ዓመት በፊት የተጀመረው ይህ አዲስ አሰራር የሰራተኞችን የመስራት አቅም ከማሳደጉ ባለፈ ተቋማትን ትርፋማ አድርጓል ተብሏል
ሳምንታዊ የስራ ቀናትን ወደ አራት ቀናት የማውረዱ እቅድ በብዙ ሀገራት ተቀባይነት እያገኘ ነው ተባለ፡፡
ከአራት ዓመት በፊት የኮሮና ቫይረስ ሲከሰት የተለመዱ የስራ ባህሎች እንዲቀየሩ አስገድዶ ነበር፡፡ ለአብነትም ከቤት ሆኖ መስራት፣ ለሰራተኞች በቂ እረፍት መስጠት፣ የስራ ሰዓትን መቀነስ እና ሌሎችም እርምጃዎች ተወስደው ነበር፡፡
የቫይረሱ ስርጭት ከቀነሰ እና ህይወት ወደ ቀድሞ መመለስ ሲጀምር ግን ከቤት ሆኖ መስራት እና ሌሎች አሰራሮች በዛው ቀጥለዋል፡፡
ሳምንታዊ አራት የስራ ቀናት ማለት ሰራተኞች ሳምንታዊ ስራቸውን ሙሉ ለሙሉ በተጠቀሱት ቀናት መስራት የሚጠበቅባቸው ሲሆን ደመወዛቸው ደግሞ አምስት ቀናት እንደሰሩ ተደርጎ ይከፈላቸዋል የሚል ነው፡፡
በተለይም ሰራተኞች የተሻለ እረፍት ሲያገኙ ተጨማሪ ስራዎችን የመስራት ፍላጎታቸው መጨመር፣ የተቋማት አትራፊነት መጨመር እና ሌሎችም ጥቅሞች እየታዩበት መምጣታቸው ተገልጿል፡፡
ይህን ተከትሎም ቤልጂየም የሰራተኞችን ምርታማነት እና የተቋማትን ውጤታማነት ለማሳደግ በሚል አራት የስራ ቀናትን ለሙከራ በተወሰኑ ተቋማት ላይ ከተገበረች በኋላ ውጤታማ ሆኖ በመገኘቱ በይፋ ሳምንታዊ የስራ ቀናትን ከአምስት ቀናት ወደ አራት ቀናት ዝቅ አድርጋለች፡፡
ሰራተኞች በሳምንት አራት ቀናት መስራት ከጀመሩ በኋላ የአዕምሮ ጤናቸው ለውጥ ማሳየቱ፣ ጫናዎችን በመፍራት ቤት ውስጥ ይውሉ የነበሩ ዜጎች የመስራት ፍላጎት ማሳየታቸው፣ የተቋማት አገልግሎት አሰጣጥ መሻሻሉን እና ሌሎችም ለውጦች እንደመጡ የሐገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር አሌክሳንደር ደ ክሮ ተናግረዋል፡፡
ዩሮ ኒውስ እንደዘገበው ከሆነ ከቤልጂየም በኋላ ብሪታንያ የአራት ስራ ቀናትን በ61 ኩባንያዎች ላይ ለስድስት ወራት ከሞከረች በኋላ ውጤታማ መሆኑን ተከትሎ ይፋዊ የስራ ቀናትን ወደ አራት ቀናት ዝቅ ለማድረግ በሂደት ላይ ነች ተብሏል፡፡
የአውሮፓ ባለግዙፍ ኢኮኖሚዋ ጀርመንም ይህን የአራት ስራ ቀናት እቅድን በሙከራ ደረጃ በመተግበር ላይ እንደሆነች ተገልጿል፡፡
ከጀርመን በተጨማሪ ስፔን፣ ፖርቹጋል፣ ስዊድን ፊንላንድ እና ሌሎችም ሀገራት የሰራተኞቻቸውን የስራ ቀናት ወደ አራት ቀናት ዝቅ ለማድረግ በሂደት ላይ እንደሆኑ በዘገባው ላይ ተጠቅሷል፡፡