ቱርክ በሊቢያ ጉዳይ የምታደርገውን ጣልቃ ገብነት ቀጥላለች በሚል በፈረንሳይ ክስ ቀረበባት
የፈረንሳይ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን በሊቢያ ጉዳይ ማንም ጣልቃ እንዳይገባ የተደረሰውን ስምምነት ቱርክ ጥሳለች በሚል የሀገሪቱን ፕሬዝዳንት ሬሲፕ ታይፕ ኤርዶአንን ከሰዋል፡፡
በዚህ ወር አጋማሽ የዓለም መሪዎች በሊቢያ የርስበርስ ጦርነት የትኛውም ሀገር ጣልቃ እንዳይገባ እና የተባበሩት መንግስታት የጦር መሳሪያ ማዕቀብ እንዲጸና ተስማምተዋል፡፡
ይሁንና በተባበሩት መንግስታት እውቅና ያለውን የናሽናል አኮርድ መንግስት የምትደግፈው ቱርክ የጦር መርከቧን ወደ ሊቢያ ልካለች ተብሏል፡፡
ኤርዶአን በፈረንሳዩ አቻቸው ለቀረበባቸው ክስ ምላሽ አልሰጡም፡፡
ከ2019 ሚያዝያ ወር ጀምሮ በጄነራል ሀፍታር የሚመራው ብሔራዊ ጦር በናሽናል አኮርድ ላይ መጠነ ሰፊ ጥቃት በመፈጸም የሀገሪቱን አብዛኛውን ክፍል ከመቆጣጠሩም ባለፈ ትሪፖሊን ለመያዝ በመዋጋት ላይ ነው፡፡
ፕሬዝዳንት ማክሮን እንደሚሉት ቱርክ የጦር መርከቧን ወደ ሊቢያ ዳርቻ መላኳ ስምምነትን ከመጣስ ባለፈ መላው አውሮፓንና የሳኸል ቀጣናን ደህንነት አደጋ ውስጥ የሚጥል ነው፡፡
ከሰሀራ በረሀ በስተደቡብ የሚገኘው የሳሄል ቀጣና የጽንፈኛ ታጣቂዎች መነሓሪያ እና የውጊያ አውድማ ነው፡፡ በስፍራው 4500 የፈረንሳይ ወታደሮች እና ከ14 ሺ በላይ የተመድ ሰላም አስከባሪዎች ይገኛሉ፡፡
ሊቢያ ወደ መረጋጋት ካልመጣች እና የጦር መሳሪያ ማዕቀቡ ካልተከበረ የተለያዩ መሳሪያዎች ወደ ሳኸል ሊሸጋገሩ እንደሚችሉ ተሰግቷል፡፡
ሙአማር ጋዳፊ በ2011ዱ ህዝባዊ አመጽ ህይወታቸው ካለፈ ወዲህ መረጋጋት ያልቻለችው ሊቢያ አሁንም የስጋት ምድር እንደሆነች ቀጥላለች፡፡
ምንጭ፡-ቢቢሲ