ተ.መ.ድ. በሊቢያ ላይ የተጣለው የጦር መሳሪያ ማእቀብ እየተጣሰ ነው አለ
የተባበሩት መንግስታት ድርጀት (ተ.መ.ድ.) በርካታ ሀገራት ከሳምንት በፊት በጀርመን በርሊን በሊቢያ ላይ የጦር መሳሪያ ማእቀብ ለመጣል የደረሱትን ስምምነት እየጣሱ መሆናቸውን ማስታወቁን ሲጂቲኤን ዘግቧል፡፡
የ ተ.መ.ድ. የሊቢያ መልእክተኛ እንደተናገሩት ከሆነ ባለፉት 10 ቀናት ዘመናዊ የጦር መሳሪያ የጫኑ በረራዎች በምእራባዊና በምስራቃዊ ሊቢያ በሚገኙ የአየር ማረፊያዎች ሲያርፉ ተስተውለዋል ብለዋል፡፡
የማእቀቡ መጣስ ሊቢያን ወደ ከፋና ወደተባባስ ጦርነት ሊያስገባት እንደሚችል ተ.መ.ድ አስጠንቅቋል፤ ማእቀቡን የትኞቹ ሀገራት እንደጣሱት ግን ግልጽ አላደረገም፡፡
የበርሊኑ ጉባኤ አላማም የሊቢያ ተፋላሚ ኃይሎች ወደ ስምምነት እንዲደርሱና የተ.መ.ድ. የመሳሪያ ማእቀብ እንዲከነር ነበር፡፡ በጉባኤው ላይ ከዩናይትድ አረብ ኤሚሬትስ፣ከግብጽ፣ ከቱርክ እንዲሁም ከአሜሪካ፣ ከፈረንሳይ፣ ከእንግሊዝና ከአዉሮፓ ህብረት የተውጣጡ ከፍተኛ ባለስልጣናት ተገኝተው ነበር፡፡
የቀድሞው የሊቢያው መሪ ሙአማር ጋዳፊ እ.ኤ.አ በ2011 ከስልጣን ከተወገዱ በኋላ ሀገሪቱ ወደ ቀዉስ ዉስጥ መግባቷ የሚታወስ ነው፡፡
በተ.መ.ድ. እውቅና ያለው የብሔራዊ ስምምነት መንግሰት በአንድ ወገን፣ በጄነራል ከሊፋ ሀፍታር የሚመራው የሊቢያ ብሔራዊ ጦር በሌላ ወገን በመሆን ሊቢያ በእርስበእርስ ጦርነት እንድትታመስ አድርገዋታል፡፡
ሁለቱ ተፋላሚ ወገኖች በጥር መጀመሪያ ሳምንት ተኩስ ለማቆም ተስማምተዋል፡፡