ፈረንሳይ ሴኔጋልን ቅኝ በገዛችበት ወቅት ጅምላ ጭፍጨፋ መፈጸሟን አመነች
የጅምላ ጭፍጨፋው የተፈጸመው በ2ኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ፈረንሳይን ለማገዝ የተጓዙ ወታደሮች ላይ ነው
ወታሮቹ “ክፍያቸው ከፈረንሳይ ወታደሮች ጋር ለምን አልተመሳሰለም” ብለው በመጠየቃቸው ነው የጅምላ ግድያው የተፈጸመባቸው
ፈረንሳይ ሴኔጋልን ቅኝ በገዛችበት ወቅት ጅምላ ጭፍጨፋ መፈጸሟን ለመጀመሪያ ጊዜ ማመኗ ተነግሯል።
ፈረንሳይ ወታደሮቿ ከ80 ዓመታት በፊት በሴኔጋል ውስጥ በደርዘን የሚቆጠሩ አሊያም በመቶዎች የሚቆጠሩ የምዕራብ አፍሪካ ወታደሮች ላይ የጅምላ ጭፍጨፋ እንደፈጸመች ማመኗን የሴኔጋል ፕሬዝዳንት ባሲሩ ዲዮማዬ ፋዬ አስታውቀዋል።
በወቅቱ የጅምላ ጭፍጨፋ የተፈጸመባቸው ወታደሮች በሁለተኛው የዓለም ጦርነት መጀመሪያ ላይ የቅኝ ገዢዋን ፈረንሳይን ለማገዝ ተቀጠረው የነበሩ የቲራይለር ሴኔጋላይስ ክፍል አባላት ነበሩ ተብሏል።
ወታደሮቹ በ1941 ወደ ሴኔጋል በሚመለሱበት ወቅት ከደመወዛቸው ጋር በተያያዘ ከፍተኛ ተቃውሞ አሰምተው እንደነበረ የሚናገሩት የታሪክ ተመራማሪዎች፤ ይህም ጭካኔ የተሞላበት ግድያ እንደፈጸምባቸው ምክንያት ነበረ።
የወታደሮቹ ግድያ በሴኔጋል እና በፈረንሣይ መካከል የክርክር ነጥብ ሆኖ የቆየ ሲሆን፤ ፈረንሳይ በሴኔጋል ጅምላ ጭፍጨፋ መፈጸሟን ከሰሞኑ አምናለች።
ፈረንሳይ ስለ ግድያው አምና እውቅና ስለ መስጠቷ የተሰማውም የሴኔጋሉ ፕሬዝዳንት ዲዮማዬ ፋዬየሀገራ ግንኙነት ዳግም እያገገመ መምጣቱን በተናገሩበት ወቅት ነው።
“ቲራይለር ሴኔጋላይስ” ጦር ክፍል ውስጥ የተካተቱት ተዋጊዎች ከሴኔጋላውያን ብቻ አልነበሩም የተባለ ሲሆን፤ በወቅቱ የፈረንሳይ ቅኝ ግዛት ስር የነበሩት የማሊ፣ ጊኒ፣ ኒጀር፣ ቤኒን እና ቻድ ወታሮችም ይገኙበት ነበር ተብሏል።
ወታሮቹ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ፈረንሳይን ለማገዝ ወደ ፈረንሳይ የተላኩ ሲሆን፤ በርካቶች ጀርመን ፈረንሳይን በወረረችበት ወቅት ተይዘው ነበር።
ወታደሮቹ በፈረንጆቹ በ1944 ነፃ የወጡ ሲሆን፤ ወደ ሴኔጋል ተወስደው ከዋና ከተማው ዳካር 15 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በሚገኘው ቲያሮዬ ወታደራዊ ካምፕ ውስጥ እንዲቀመጡ መደረጉም ይነገራል።
ወታሮቹ ፈረንሳይን ለቀው ከመውጣታቸው በፊትም ብዙዎች ሊከፈላቸው የተዘጋጀው ክፍያ ከሌሎች የፈረንሳይ ወታደሮች ጋር ተመሳሳይ ባለመሆኑ ቅሬታ ሲያሰሙ እንደነበር የታሪክ ምሁር አርሜሌ ማቦን ተናግረዋል።
“ታህሳስ 1 ላይ ፈረንሳዮች ተቃውሞውን በኃይል አስቆሙት” የሚሉት የታሪክ ምሁሩ፤ በወቅቱ አመጹን ለማስቆም ከቲራይለር ሴኔጋላይስ ውስጥ 35 ያህሉ ገድላለች ቢባልም፤ አንዳንዶች ግን የሟቾች ቁጥር 400 ይደርሳል ይላሉ።
ስኔጋል “ቲራይለር ሴኔጋላይስ” ላይ የጅምላ ጭፍጨፋ የተፈጸመበትን ቀን ፊታችን እሁድ ታህሳስ 1 ቀን 80ኛ ዓመቱን ለማክበር እየተዘጋጀች ነው ተብሏል።