የዩክሬን መልሶ ማጥቃት እንደ ሆሊውድ ፊልም በፍጥነት አያልቅም - ዜለንስኪ
ፕሬዝዳንቱ በደቡብ እና ምስራቅ ግንባር ድል እያገኘን ነው ቢሉም አጠቃላይ የመልሶ ማጥቃቱ ዘገምተኛ መሆኑን ገልጸዋል
ሩሲያ በበኩሏ ኬቭ የመልሶ ማጥቃት ዘመቻ ለመጀመር እስካሁን ቁርጥ ያለ አቋም መያዝ ተስኗታል ብላለች
የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮልድሚር ዜለንስኪ ሀገራቸው በሩሲያ ላይ የጀመረችው የመልሶ ማጥቃት እርምጃ ከሚጠበቀው አንጻር አዝጋሚ መሆኑን ተናግረዋል።
ፕሬዝዳንቱ ከቢቢሲ ጋር በነበራቸው ቆይታ የሩሲያ ሃይሎች ከ200 ሺህ ስኩዌር ኪሎሜትር በላይ መሬት የዩክሬንን ድንበር መክበባቸውን ነው ያነሱት።
በመሆኑም ኬቭ የምትወስደው እርምጃ በሩሲያ በተያዙ አካባቢዎች የሚገኙ ዩክሬናውያንን ህይወት አደጋ ላይ እንዳይጥል ጥንቃቄ እንደሚደረግ አብራርተዋል።
“አንዳንዶች ይህን (የመልሶ ማጥቃት ዘመቻ) እንደሆሊውድ ፊልም ይመለከቱትና አሁኑኑ ድል ይሻሉ፤ ነገር ግን እንደዛ አይደለም” ብለዋል ዜለንስኪ።
ዩክሬን ፈጣን የመልሶ ማጥቃት እንድታደርግ ፍላጎቱና ጫናው ቢበዛም ባሰብነው መንገድ የመልሶ ማጥቃት እርምጃ እንወስዳለን ሲሉም ተደምጠዋል።
በደቡባዊ እና ምስራቃዊ ዩክሬን ስምንት መንደሮችን ከሩሲያ ማስለቀቃቸውን በመጥቀስም የሩሲያ ሃይሎች ከዩክሬን ሳይወጡ ምንም አይነት ድርድር አናደርግም ብለዋል።
የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን በበኩላቸው፥ ኬቭ በአውደ ውጊያዎች እየተሸነፈች መሆኑን ነው የተናገሩት።
ኬቭ መልሶ ማጥቃት ለመጀመር እስካሁን ቁርጥ ያለ አቋም መያዝ እንደተሳናትና በአንዳንድ አካባቢዎች ማፈግፈግን መምረጧንም አብራርተዋል።
የሩሲያው ቅጥረኛ ወታደራዊ ቡድን ዋግነር መሪው ይቪግኒ ፕሪጎዢን ግን ከፑቲን የተቃረነ ሃሳብ አላቸው።
“ሩሲያ በዩክሬን ሽንፈት እያጋጠማት ነው፤ በርካታ አካባቢዎችንም ለቃለች፤ ግን እውነቱ ለሩሲያ ህዝብ አይነገረውም” ሲሉም የድምጽ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
ዩክሬን የመልሶ ማጥቃት ዘመቻዋ ለምን ተጓተተ?
ወታደራዊ ተንታኞች ኬቭ ከምዕራባውያን ቃል የተገቡላት የጦር መሳሪያዎች በብዛት እስኪገቡ የመልሶ ማጥቃት ዘመቻውን ገታ ሳታደርገው እንዳልቀረች ያምናሉ።
በተለይም በሞስኮ የበላይነት የተያዘባትን የአየር ጥቃት ለመመከት እና አጻፋውን ለመመለስ የጸረ ሚሳኤልና የጦር ጄቶች ድጋፍ በእጅጉ እንደሚያስፈልጋትም ይገልጻሉ።
በዚህና በሌሎች ምክንያቶች ለወራት ሲጠበቅ የነበረው የመልሶ ማጥቃት ዘመቻ በሚፈለገው ፍጥነት እየሄደ እንዳልሆነ ነው በዋሽንግተን ዲሲ የሚገኘው የአለም የጦርነት ጉዳዮች ጥናት ተቋም (አይ ኤስ ደብሊው) የሚጠቅሰው።
ኬቭ ከዚህ ቀደም በሩሲያ የተያዙባትን አካባቢዎች ዳግም ለማስመለስ አስፈላጊውን ሁሉ ዝግጅት ማድረጓን መግለጿ ይታወሳል።
ይሁን እንጂ በአውደ ውጊያ እየታየ ያለው ነገር ዝግጅቷ ብዙ የሚቀረው ነገር እንዳለ ያሳያል ይላሉ የሩሲያ ተንታኞች።