አውሮፓ ከአሜሪካ ተጽዕኖ ልትላቀቅ እንደሚገባ ፕሬዝዳንት ማክሮን ተናገሩ
አውሮፓ ሶስተኛ የዓለም አማራጭ የመሆን እድሏን ልትጠቀም እንደሚገባ ፕሬዝዳንቱ ገልጸዋል
ቻይና ከስጋትነት ይልቅ የአውሮፓ ተጨማሪ አጋር ልትሆን ትችላለች ተብሏል
አውሮፓ ከአሜሪካ ተጽዕኖ ልትላቀቅ እንደሚገባ ፕሬዝዳንት ማክሮን ተናገሩ፡፡
የፈረንሳይ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን እና የአውሮፓ ህብረት ኮሚሽን ኡርሱላ ቮንደረሊን ወደ ቻይና አቅንተው ከፕሬዝዳንት ሺ ጅምፒንግ ጋር መምከራቸው ይታወሳል፡፡
ፐሬዝዳንት ማክሮን የቤጂንግ ቆይታቸውን አጠናቀው ወደ ሀገራቸው እየተመለሱ ባሉበት አውሮፕላን ውስጥ የነበረው የፖለቲኮ ጋዜጠኛ ቃለመጠይቅ አድርጎላቸው እንደነበር ተገልጿል፡፡
ፕሬዝዳንቱ በዚህ ጊዜ እንዳሉት አውሮፓ በአሜሪካ ላይ ጥገኛ መሆኗን ያመኑ ሲሆን ይህ ግን ትክክል አለመሆኑን እና ሊስተካከል ይገባል ብለው እንደሚያምኑ ተናግረዋል፡፡
የአውሮፓ ሀይል አቅርቦት፣ የጦር መሳሪያ ቴክኖሎጂ፣ የዓለም ንግድ እና ሌሎች ግንኙነቶች ሁሉ በአሜሪካ የበላይነት የተያዙ መሆናቸውን በዘገባው ላይ ተጠቅሷል፡፡
ፕሬዝዳንቱ አክለውም አውሮፓ የአሜሪካ እና ቻይና ሀይል ሚዛን ማስጠበቂያ ሊሆኑ አይገባም ያሉ ሲሆን አውሮፓ በራሷ ልትቆም እንደሚገባ ተናግረዋል ተብሏል፡፡
የዓለም መሪነትን ዋሸንግተን እና ቻይና ቢቆጣጠሩም አውሮፓ ሶስተኛዋ ባለ ተጽዕኖ እንድትሆን ብራስልስ ቤጂንግን እንደ ስጋትነት ሳይሆን እንደ አጋር ማየት የሚያስፈልግበት ወቅት መሆኑንም ፕሬዝዳንቱ መናገራቸው በዘገባው ላይ ተጠቅሷል፡፡
አውሮፓ ያጋጠማትን ጦርነት በራሷ መፍታት የምትችልበት አቅም እንደሌላት ፕሬዝዳንት ሺ ፒንግ ቤጂንግን ለጎበኙት ፕሬዝዳንት ማክሮን እና ቮንደርሊን እንደተናገሩ እንዲሁም የታይዋን ጉዳይ የቻይና የውስጥ ጉዳይ መሆኑን በአንክሮ መናገራቸም ተገልጿል፡፡
ዋሸንግተን በተለይም ቻይናን፣ ሩሲያን እና ኢራንን ለመጉዳት በሚል ማዕቀብ መጣሏ የአውሮፓን ንግድ በአሜሪካ ላይ ብቻ እንዲመሰረት እና በማዕቀቦቹ የአውሮፓ ኩባንያዎችም ሁለተኛ ተጎጂ እንዲሆን አድርጓል ብለዋል ተብሏል፡፡