በጉባኤው ላይ ለመሳተፍ ጥያቄ ያቀረበችው ፈረንሳይ ከቡድን ሰባት ሀገራት የመጀመሪያ ሆናለች
ፈረንሳይ በደቡብ አፍሪካው የብሪክስ ጉባኤ ላይ ለመሳተፍ ጠየቀች።
በብራዚል፣ ሩሲያ፣ ሕንድ፣ ቻይና እና ደቡብ አፍሪካ የተመሰረተው ብሪክስ በፈረንጆቹ 2009 ነበር የተመሰረተው።
በምዕራባዊያን የበላይነት የተያዘውን የዓለም ስርዓት ለመቀየር አልያም አማራጭ የዓለም ስርዓት መፍጠር የስብስቡ አላማ እንደሆነ በተደጋጋሚ ይገለጻል።
የቡድን ሰባት አባል ሀገር የሆነችው ፈረንሳይ ደግሞ የፊታችን ነሀሴ በደቡብ አፍሪካ በሚካሄደው የብሪክስ የመሪዎች ጉባኤ ላይ ለመሳተፍ ጥያቄ ማቅረቧን ቢቢሲ ዘግቧል።
እንደዘገባው ከሆነ ፈረንሳይ በጉባኤው ላይ ለመሳተፍ ለወቅቱ የብሪክስ ሊቀመንበር ደቡብ አፍሪካ በይፋ ጥያቄ አቅርባለች።
የፈረንሳይ ውጪ ጉዳይ ሚንስትር ካትሪን ኮሎና ከደቡብ አፍሪካ አቻቸው ናለዲ ፓንደር ጋር ተወያይተዋል።
የደቡብ አፍሪካ ፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፎዛ በቀጣዮቹ ሳምንታት ወደ ፓሪስ አቅንተው ከፈረንሳይ አቻቸው ኢማኑኤል ማክሮን ጋር እንደሚመክሩ ይጠበቃልም ተብሏል።
ብሪክስ አሁን ላይ አዲስ የዓለም ስርዓት ለመፍጠር በመጨረሻው ምዕራፍ ላይ መሆኑን ከሁለት ሳምንት በፊት ባካሄደው የውጭ ጉዳይ ሚንስትሮች ስብሰባውን ባካሄደበት ወቅት ገልጿል።
በርካታ የዓለማችን ሀገራት ብሪክስን ለመቀላቀል ጥያቄ በማቅረብ ላይ ሲሆኑ ሳውዲ አረቢያ፣ ቱርክ፣ ኢራን፣ የተባበሩት አረብ ኢምሬት፣ ግብጽ እና ሌሎችም ተጠቃሽ ናቸው።