ፑቲን ሩሲያውያን በነቂስ ወጥተው ድምጽ እንዲሰጡ ጥሪ አቅርበዋል
በሩሲያ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ በዛሬው እለት ድምጽ የመስጠት ስነ ስርዓት ተጀምሯል።
ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ከፍተኛ የአሸናፊነት ግምት ያገኙበት የሩሲያ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ድምጽ አሰጣጥ ስነ ስርዓት እስከ እሁድ መጋት 8 ቀጥሎ ይካሄዳል።
ምርጫው በመላው ሩሲያ እንዲሁም ሩሲያ በቅርቡ ከዩክሬን ወደ ራሷ በቀላቀለቻቸው ክልሎቸም ጭምር እየተካሄደ መሆኑም ነው የተገለጸው።
በሞስኮ ሰልፍ በበዛባቸው የምርጫ ጣቢያዎች ላይም በአካል ከሚደረግ ምርጫ በተጨማሪ በኦን ላይን አማራጭ ድምጽ እየተሰጠ መሆኑ ተነግሯል።
የሩሲያ ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ትናንት ምሽት በቪዲዮ ባስተላለፉት መልእክት ሩሲያውያን በነቂስ ወጥተው ድምጽ እንዲሰጡ ጥሪ አቅርበዋል።
“የስልጣን ምንጭ ህዝብ ነው” ያሉት ፑቲን፤ “ይህ ማለት የአባት ሀገር ሩሲያን ወደፊት እጣ ፈንታ የሚወስኑት የሩሲያ ዜጎች ናቸው” ሲሉም ተናግረዋል።
“ሀገሪቱ በጣም አስቸጋሪ እና ፈታኝ በሆነ ጊዜ ውስጥ እያለፈች ነው” ያሉት ፕሬዝዳንት ፑቲን፤ ይህንን ለማለፍ በከፍተኛ የራስ መተማመን እና በአንድነት መቆም ያስፈልጋል ብለዋል።
“የአባቶቻችን ሀገር በመጠበቅ ላይ ያሉ ጀግኖች የሀገሪቱ የጦር ሰራዊት አባላትም በዚህ ምርጫ ላይ ባሉበት ሆነው ድምጽ ይሰጣሉ” ሲሉም ፑቲን ተናግረዋል።
“በቀጣይ ሶስተ ቀናት ውስጥ ሁሉም ሩሲያውያን የመምረጥ መብታቸውን ሊጠቀሙ ይገባል” ሲሉም ፕሬዝዳንት ፑቲን ጥሪ አቅርበዋል።
በሩሲያ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ላይ ከቭላድሚር ፑቲን በተጨማሪ የክሬምሊንን ቁልፍ ሰልጣን ለመቆጣጠር ተስፋ ያደረጉ ሶስት እጩዎች "የማይቻለውን ውድድር" ተቀላቅለዋል።
የሩሲያ ማዕከላዊ ምርጫ ኮሚሽን ከፑቲን ጋር የሚፎካከሩ ሶስት እጩዎችን መመዝገቡን ያስታወቀ ሲሆን፤ እጩዎቹም ቭላዲስላቭ ዳቫንኮቭ፣ ሊዮኒድ ስሉትስኪ እና ኒኮላይ ካሪቶኖቭን ናቸው ተብሏል።
በምርጫው ለፑቲን ከፍተኛ ተፎካካሪ ይሆናሉ ተብለው ተጠብቀው የነበሩት ዋነኛው ተቃዋሚ በእጩነት ሳይቀርቡ ቀርተዋል ነው የተባለው።
የሩሲያ ማዕከላዊ ምርጫ ኮሚሽን ዋነኛውን የተቃዋሚ ተፎካካሪ ቦሪስ ናድዘሀዲን ከፉክክሩ ውጪ ያደረገው ፊርማ በማሰባሰብ ሂደት ለይ የማጭበርበር ተግባር ተገኝቶባቸዋል በሚል ነው።