በፈረንሳይ ኤርፖርት ለ18 ዓመታት የኖረው ኢራናዊ ህይወቱ አለፈ
ሜህራን ናስሪ የተባለው የዚህ ኢራናዊ ታሪክ በሆሊውድ አማካኝነት ወደ ፊልምነት ተቀይሯል
ግለሰቡ ከ18 ዓመታት በፊት አናቱን ለመፈለግ በሚል ነበር ወደ አውሮፓ የመጣው
በፈረንጆቹ 1988 ላይ እናቱን ፍለጋ ወደ አውሮፓ የገባው ሜህራን ናስሪ የተሰኘው ይህ ኢራናዊ የበርካቶችን ትኩረት ስቦ ቆይቷል።
ግለሰቡ እናቱን ፈልጎ ወደ ፈረንሳይ ይምጣ እንጂ ህጋዊ ሰነድ በእጁ ላይ ባለመያዙ ምክንያት የሞሪያ ፈቃድ እና ሌሎች የመንቀሳቀሻ ፈቀድ ሊያገኝ አልቻልም።
በዚህም ምክንያት በፈረንሳየ ቻርልስ ደጎል ኤርፖርት ተጠልሎ ላለፉት በርካታ ዓመታት ተጠልሎ ሲኖር ታሪክ በብዙሃን መገናኛዎች መሰራጨቱን ተከትሎ የፊልም ሰሪዎችን ትኩረት ለመሳብ በቅቷል።
በዚህ ኢራናዊ የህይወት ታሪክ ላይ ያተኮረ ዘ ተርሚናል የተሰኘ ፊልም የተሰራ ሲሆን ቶም ሀንክስ የተወነበት ይህ ፊልም በፈረንጆቹ 2004 ላይ ተሰርቶ ለተመልካች መቅረቡ ይታወሳል።
ይህ ግለሰብ በመጨረሻም ከፈረንሳይ የመኖሪያ ፈቃድ ያገኘ ቢሆንም ከጥቂት ሳምንታት በፊት ወደ ነበረበት ቻርልስ ደጎል ኤርፖርት ተመልሶ ህይወቱ እስካለፈበት ጊዜ እንደኖረ ኤ.ኤፍ.ፒ ዘግቧል።
ናስሪ በኢራን ኩዝስታን በፈረንጆቹ 1945 የተወለደ ሲሆን እናቱን ፍለጋ በሚል መጀመሪያ ወደ ቤልጂየም፣ እንግሊዝ፣ ኔዘርላንድ እና ጀርመን የተጓዘ ቢሆንም የጉዞ ሰነዶችን አልያዝክም በሚል ከሁሉም ሀገራት እንደተባረረ ተገልጿል።
በመቀጠልም ወደ ፈረንሳይ በመምጣት ላለፉት 18 ዓመታት ስለራሱ ህይወት ሲጽፍ፣ መጽሃፍትን እና ጋዜጦችን በማንበብ ህይወቱን ሲያሳልፍ ቆይቷል ተብሏል።
እራሱን ሰር አልፍሬድ በሚል የሚጠራው ይህ ኢራናዊ የበርካታ ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ትኩረት መሳቡን ተከትሎ በቀን በአማካኝ ከስድስት ሚዲያዎች ጋር ቃለ መጠይቅ እንደሚያደርግ ተገልጿል።
ግለሰቡ በፈረንጆቹ 1999 ላይ ከፈረንሳይ መንግስት የመኖሪያ ፈቃድ ቢያገኝም እስከ 2006 ድረስ በዚያው በኤርፖርት አሳልፏል።
በመቀጠልም ህመም ሲያጋጥመው ወደ ሆስፒታል የተወሰደ ሲሆን በሱ ታሪክ ላይ ካነጣጠረው ፊልሙ ላይ በተከፈለው ገንዘብ ሆቴል ቢቆይም ከጥቂት ሳምንታት በፊት ወደ ቻርልስ ደጎል ኤርፖርት ተመልሶ እንደነበር ተገልጿል።
ነስሪ ህይወቱ አልፎ በተገኘበት በዚህ ኤርፖርት ውስጥ በሺዎች የሚቆጠር ዩሮ በእጁ ላይ መገኘቱን ዘገባው ጠቅሷል።