ቲክቶክ የኳታሩን የአለም ዋንጫ አድምቆ ለበርካቶች ሲሳይ ሆኗል
የአለም ዋንጫው ከተጀመረ ወዲህ በፊፋ የአለም ዋንጫ ሃሽታግ የተለቀቁ ቪዲዮዎች ከ12 ቢሊየን ጊዜ በላይ ታይተዋል
የኳታሩን የአለም ዋንጫ ያልታዩ ክስተቶች በስልክ ካሜራቸው ለማስቀረት ዶሃ የገቡ ቲክቶከሮችም በሚሊየን ተከታይ ማፍራት ችለዋል
የቻይናው ባይትዳንስ ኩባንያ ንብረት የሆነው ቲክቶክ ከፌስቡክ እና ኢንስታግራም ቀጥሎ በርካቶች የሚጎበኙት የማህበራዊ ትስስር ገጽ ሆኗል።
በወር 1 ቢሊየን ቋሚ ደንበኞች አሉኝ በሚለው ቲክቶክ በየቀኑ ክ1 ሚሊየን በላይ ቪዲዮዎች ይታያሉ።
የቲክቶክ ተጠቃሚዎች በቀን በአማካይ 48 ደቂቃዎችን በ60 ሰከንድ ቪዲዮዎች ላይ እንደሚያሳልፉ ነው ጥናቶች የሚያሳዩት።
በየጊዜው በደንበኞቹ ብዛት ከሜታ ኩባንያ ጋር መፎካከር የጀመረው ቲክቶክ የኳታሩ የአለም ዋንጫ ተደራሽነቱን ይበልጥ አስፍቶለታል ነው የተባለው።
ቲክቶክ ከ2018ቱ የሩስያ የአለም ዋንጫ በተለየ መልኩ ለኳታር የአለም ዋንጫ ልዩ ድምቀት መስጠቱ ተገልጿል።
ከእንግሊዝ ብሄራዊ ቡድን ተጫዋቹ ቡካዮ ሳካ “የፊደል ትምህርት ቤት’’ እስከ የጨዋታ ግምቶችን የሚያጋሩ ቲክቶከሮች ድረስ በየእለቱ በስታዲየሞች የሚታዩ ልዩ ክስተቶች በትስስር ገጹ በስፋት ሲጋራ ቆይቷል።
የፊፋ የአለም ዋንጫ በሚል ሃሽታግ የተለጠፉ ቪዲዮዎች ከ12 ቢሊየን ጊዜ ታይተዋል መባሉም የቲክቶክን ተደራሽነት ያመላክታል።
በሩብ ፍጻሜው የተገናኙት የእንግሊዝና የፈረንሳይ ብሄራዊ ቡድኖች ብቻ ከ1 ሚሊየን በላይ ተከታዮችን በዚህ የአለም ዋንጫ አግኝተዋል።
የሀገራቱ ብሄራዊ ቡድኖች ብቻ ሳይሆን የአለም ዋንጫውን ልዩ ልዩ ገጽታዎች በስልኮቻቸው ቀርጸው ለማስተላለፍ ፈቃድ ጠይቀው ይሁንታን ያገኙ በርካታ ቲክቶከሮችም አጋጣሚው በእጅጉ ጠቅሟቸዋል።
የአለም ዋንጫው ከተጀመረ ወዲህ የለቀቃቸው ቪዲዮዎች ከ170 ሚሊየን በላይ ጊዜ የታየለት የ24 አመት ወጣት ቤን ብላክ አንዱ የበረከቱ ተጠቃሚ ነው።
በዳንስ እያዋዛ በሚለቃቸው መልዕክቶች የሚታወቀው የ19 አመቱ ጁኒየር ፕሬራም በኳታር የአለም ዋንጫ ምክንያት ከ2 ሚሊየን በላይ አዳዲስ ተከታዮችን አግኝቷል።
ከነዚህ ቲክቶከሮች ባሻገር የተለያዩ ድርጊታቸው አለም አቀፍ እውቅና ያስገኘላቸው ግለሰቦችም የዝና ከፍታ ላይ ያወጣቸው ቲክቶክ ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም።
ኬንያዊው የባቡር አቅጣጫ ጠቋሚም ሆነ የሳኡዲን በአርጀንቲና መሸናፍ ተከትሎ በቀጥታ ስርጭት የነበረን ጋዜጠኛ “ ሜሲ የት ነው’’ እያለ እስከሚጠይቀው ግለሰብ ቢሊየኖች የተመለከቷቸው ቅንጭብጭብ ሁነቶች በቲክቶክ በኩል ለአለም ደርሰዋል።
ይህም የዶሃውን ዝግጅት በልዩ ድባብ ከመሙላቱ ባሻገር ለበርካቶች የእንጀራ ምንጭ መሆኑ ተነግሯል።