ፈረንሳይ የሀገሯንና የአውሮፓ ህብረት ዜጎችን ከኒጀር ማስወጣት ልትጀምር ነው
የወታደሩ ደጋፊዎች የፈረንሳይን ባንዲራ በማቃጠል ኢምባሲው ላይ ጥቃት ሰንዝረዋል
የኒጀር መፈንቅለ መንግስት በሳህል አካባቢ ድንጋጤን ፈጥሯል
በምዕራብ አፍሪካዊቷ ሀገር ኒጀር ወታደራዊው ጁንታ ስልጣኑን ከተቆጣጠረ ከቀናት በኋላ ፈረንሳይ የሀገሯን እና የአውሮፓ ዜጎቿን ከማክሰኞ ጀምሮ እንደምታስወጣ የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር አስታውቋል።
ባለፈው ረቡዕ ወታደራዊ መኮንኖች ፕሬዝዳንት ሞሃመድ ባዙምን እና በዲሞክራሲያዊ መንገድ የተመረጠውን መንግስታቸውን ከስልጣን ካስወገዱ በኋላ፤ የኒጀር ድንበሮች ተዘግተዋል።
የኒጀር መፈንቅለ መንግስት በምዕራብ እና መካከለኛው አፍሪካ ከሦስት ዓመታት ባነሰ ጊዜ ውስጥ ሰባተኛው ነው።
ሮይተርስ እንደዘገበው መፈንቅለ መንግስቱ በሳህል አካባቢ ድንጋጤን ፈጥሯል።
ምዕራባውያን አጋሮች ኒጀርን በሩሲያ ተጽዕኖ እንዳያጡ በስጋት የተሸበቡ ሲሆን፤ ከእስላማዊ መንግስት እና ከአልቃይዳ ጋር ግንኙነት ያላቸው ቡድኖች በአካባቢው እየበዙ በመምጣታቸው የጸጥታ ስጋት ፈጥሯል።
ፈረንሳይ ለ10 ዓመታት በሳህል ውስጥ እስላማዊ አማጺያንን ለመዋጋት የሚረዱ ወታደሮች ነበሯት።
እሁድ እለት የጁንታው ደጋፊዎች የፈረንሳይን ባንዲራ በማቃጠል በኒጀር ዋና ከተማ ኒያሚ የሚገኘውን የፈረንሳይ ኤምባሲ አጥቅተዋል።
"በኒያሚ ያለውን ሁኔታ፤ ከትናንት በስቲያ በኤምባሲያችን ላይ የተፈጸመው ሁከት፣ የአየር ክልሉ መዘጋቱና ዜጎቻችን በራሳቸው መንገድ መውጣት የማይችሉ መሆናቸውን ከግምት ውስጥ በማስገባት ፈረንሳይ ዜጎቿን እና የአውሮፓ ዜጎቿን ለቀው እንዲወጡ እያዘጋጀች ነው " ሲል የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር በመግለጫው ተናግሯል።
የሚንስቴሩ ድረ ገጽ በ2022 በኒጀር ከአንድ ሽህ 200 ገደማ የፈረንሳይ ዜጎች ነበሩ። ነገር ግን ሌ ሞንዴን ጨምሮ የፈረንሳይ መገናኛዎች እንደተናገሩት በአሁኑ ጊዜ ብዙ ቤተሰቦች እረፍት ላይ በመሆናቸው በሀገሪቱ ውስጥ ወደ 600 የሚጠጉ ዜጎች ብቻ ይገኛሉ።
ጣሊያንም ዜጎቿን ከዋና ከተማዋ ኒያሜ ለማስወጣት ልዩ በረራ እንደምታቀርብ ተናግራለች።