በኒጀር ያለው የፈረንሳይ እና አሜሪካ ጦር በእገታ ላይ ያሉትን ፕሬዝዳንት ለመታደግ ጥቃት ይከፍት ይሆን?
ኢኮዋስ በበኩሉ ስልጣን የተቆጣጠረው የኒጀር ወታደር ስልጣኑን ካላስረከበ ወታደር እንደሚያዘምት ዝቷል
የዓለም ሰባተኛ ዩራኒየም አምራቿ ኒጀር የፈጸመችው መፈንቅለ መንግሥት እንደ ማሊ እና ቡርኪናፋሶ ላይሆን ይችላል ተብሏል
በኒጀር ያለው የፈረንሳይ እና አሜሪካ ጦር በእገታ ላይ ያሉትን ፕሬዝዳንት ለመታደግ ጥቃት ይከፍት ይሆን?
በምዕራብ አፍሪካዊቷ ኒጀር ባሳለፍነው ሳምንት መፈንቅለ መንግሥት መፈጸሙ ይታወሳል።
መፈንቅለ መንግሥቱ የተፈጸመው ፕሬዝዳንት መሀመድ ባዙም በቤተ መንግስታቸው ባሉበት ነው የተባለ ሲሆን ጀነራል አብዱራህማን ቲያኒ ደግሞ የመፈንቅለ መንግስቱ አቀነባባሪ ነበሩ።
ከፈረንጆቹ 2011 ጀምሮ የኒጀር ፕሬዝዳንት ጥበቃ ጦር አዛዥ የሆኑት ጀነራል ቲያኒ ራሳቸውን የኒጀር ጦር መሪ አድርገው ሾመዋል።
ጀነራሉ ስልጣን መቆጣጠራቸውን ተከትሎ የአፍሪካ ህብረት፣ የምዕራብ አፍሪካ የኢኮኖሚክ ማህበረሰብ ወይም ኢኮዋስ እንዲሁም የአውሮፓ ህብረት አሜሪካም ድርጊቱን አውግዘዋል።
ከውግዘቱ ባለፈም ኢኮዋስ ስልጣን የተቆጣጠረው የኒጀር ወታደራዊ ቡድን በአንድ ሳምንት ውስጥ ስልጣኑን በምርጫ ስልጣን ለተቆጣጠረው ፕሬዝዳንት ባዙም መንግሥት እንዲመልስ አሳስቧል።
በጀነራል ቲያኒ የሚመራው ወታደራዊ ሀይል በሰባት ቀናት ውስጥ ስልጣን ካላስረከበ የኢኮዋስ አባል ሀገራት የተውጣጣ ሀይል ወደ ኒያሚ እንደሚገባ አስጠንቅቋል።
ስልጣኑን በመፈንቅለ መንግስት የተነጠቀው የፕሬዝዳንት ባዙም መንግስት የፈረንሳይ እና አሜሪካ ዋነኛ አጋር መሆኑን ተከትሎም መፈንቅለ መንግሥቱ ሊቀለበስ ይችላል ተብሏል።
በተለይም በኒጀር የሰፈረው የፈረንሳይ እና አሜሪካ ጦር ስልጣን በተቆጣጠረው የኒጀር ወታደራዊ ቡድን ላይ ጥቃት ሊከፍት ይችላል ተብሎም ተሰግቷል ሲል ሮይተርስ ዘግቧል።
በጀነራል ቲያኒ የሚመራው የኒጀር ወታደራዊ ቡድን በበኩሉ ፈረንሳይ የቀድሞው ፕሬዝዳንት ባዙምን ወደ ስልጣን ለማስመለስ እንቅስቃሴ ጀምራለች ሲል ወቅሷል።
ይሁንና ፈረንሳይ በኒጀር የቀረበባትን ክስ ስለመቃወሟ አልያም ስለማመኗ ከመናገር ይልቅ በኒጀር ያሉ ዜጎቿን እና ጥቅሞቿን ከጉዳት ለመጠበቅ እየተንቀሳቀሰች መሆኗን ተናግራለች።
ጀነራል ቲያኒ አክለውም ፈረንሳይን ጨምሮ የውጭ ሀይሎች የቀድሞ ፕሬዝዳንት ባዙምን ወደ ስልጣን ለመመለስ ቢሞክሩ ከባድ የደም መፋሰስ እንደሚያጋጥም አስጠንቅቋል።
ኢኮዋስ የቻዱን ፕሬዝዳንት መሀማት እድሪስ ዴቢን ወደ ኒያሚ የላከ ሲሆን በእስር ላይ ያሉት የቀድሞ ፕሬዝዳንት ባዙም ከኢኮዋስ ልዑክ ጋር ተገናኝተዋል።
ይሁንና የቻዱ ፕሬዝዳንት እና የኢኮዋስ ተወካዩ ዴቢ በእስር ላይ ካሉት ባዙም ጋር ስለምን እንደተወያዩ የተገለጸ ነገር የለም።