ተቋማቱ የተቀጡት የሃገሪቱን የመረጃ ደህንነት ህግ በመጻረር ተጠቃሚዎችን ተከታትለዋል በሚል ነው
ፈረንሳይ ጎግል እና ፌስቡክ ተጠቃሚዎቻቸውን እየሰለሉ ነው በሚል ቀጣች፡፡
ተቋማቱ የተቀጡት የተጠቃሚዎችን መረጃ ለመከታተል በሚል አጠራጣሪ የሆኑ መንገዶችን ('ኩኪዎችን') እየተጠቀሙ ነው በሚል ነው፡፡
የደንበኞቻቸውን የግላዊ መረጃ ደህንነት አልጠበቁም ያለው የፈረንሳይ የመረጃ ነጻነት ኮሚሽን (CNIL) ተቋማቱ በድምሩ 237 ሚሊዮን ዶላር እንዲቀጡ አዟል፡፡
ኮሚሽኑ ጎግል 197 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዶላር ፌስቡክ ደግሞ 68 ነጥብ 7 ሚሊዮን ዶላር እንዲከፍሉ ነው ያዘዘው፡፡
ቅጣቱን በሶስት ወራት ውስጥ እንዲከፍሉ አለበለዚያ በየቀኑ የ113 ሺ ዶላር ቅጣት እንደሚጠብቃቸው አስታውቋል፡፡
ተጠቃሚዎች የተለያዩ የድረ ገጽ እና ሌሎችንም የበይነ መረብ አገልግሎቶች ማግኘት ሲጀምሩ መረጃዎቹ በጥቃቅን መረጃዎች 'ኩኪዎች' መልክ ተከማችተው ይቀመጣሉ፡፡
'ኩኪዎች' ተጠቃሚዎች ምን ሲያደርጉ እንደነበር በቀላሉ ለመለየት ያስችላሉ፡፡ አገልግሎት ሰጪ ተቋማትም የተጠቃሚዎችን እንቅስቃሴ ከመከታተል ባለፈ ምን እንደሚፈልጉ አውቀው ማስታወቂያዎችን ለመስራት ወይም ሌሎች እርምጃዎችን ለመውሰድ ይችላሉ፡፡
ይህን ነው ኮሚሽኑ የተጠቃሚዎችን ግላዊ መብት ይጋፋል በሚል ተገቢ አይደለም ሲል የከለከለው፡፡
ጎግል እና ፌስቡክ ተጠቃሚዎች 'ኩኪዎችን' ትተው ከማለፍ ይልቅ እንዲቀበሉ እንደሚያስገድዱም ነው የገለጸው፡፡
ይህ የፈረንሳይን የመረጃ ደህንነት ህግ የሚቃረን ነውም ብሏል፡፡ ተቋማቱም ይህን ህግ አክብረን ለመስራት ዝግጁ ነን ብለዋል፡፡