ድሮኑን በመጠቀም እስከ ፈረንጆቹ 2024 ድረስ 100 ሚሊየን ዛፎችን ለመትከል ታቅዷል
የአውስትራሊያ ባዮ ቴክ ኩባንያ የደን መመናመንን በአጭር ጊዜ ሊያስቀር ይችላል ያለውን የሰው አልባ ባራሪ (ድሮን) ቴክኖሎጂ ይዞ ብቅ ብሏል።
ኩባያው አዲስ ይዞት የቀረበው ቴክኖሎጂ ዛፎችን የሚተክል ድሮን ሲሆን፤ ድሮኑ አየር ላይ እያለ ዛፎችን መትከል የሚችል መሆኑንም የሮይተርስ ዘገባ ያመለክታል።
ድሮኑ የዛፍ ዘሮችን ከሰማይ ላይ ወደ ምድር በመተኮስ እንዲተከል ያደርጋል የተባለ ሲሆን፤ ይህ የድሮን ቴክኖሎጂ በዓመት በሚሊየን የሚቆጠሩ ዛፎችን ለመትከል የሚያስችል ነው ተብሏል።
ድሮኑን ዲዛይን ያደረገው የአውስትራሊያው ኤርሲድ ኩባንያ፤ ዘር ጣዩ ድሮን በቀን እስከ 40 ሺህ ዛፎችን መትከል የሚችል መሆኑን አስታውቋል።
ኤርሲድ ኩባንያ ዋና ስራ አስፈጻሚ አንድሪው ዋከር፤ ድሮኖቹ በሙሉ አቅማቸው እንዲሰሩ ማድረግ ከተቻለ እያንዳንዱ ድሮን በቀን 40 ሺህ ዛፎችን መትከል ይችላል ብለዋል።
ይህንም ከተለምዶው ወይም ባህላዊው የዛፍ ተከላ ጋር ሲነጻጸር በ25 እጥፍ የሚፈጠን ነው ያሉት ዋና ስራ አስፈጻሚው፤ ከዋጋ አንጻርም ሲታይ እስከ 80 በመቶ የሚደርስ ቅነሽ አለው ሲሉም ተናግረዋል።
ዛፍ ተካዩ ድሮን አርቴፊሸል እንተለጀንስ እና የድሮን ቴክኖሎጂን አንድ ላይ ጠምሮ የያዘ ነው ያሉ ሲሆን፤ የዛፍ ዘሮችን ከሰማይ ላይ ወደ ምድር በመተኮስ ይተክላልም ብለዋል።
በቴክኖሎጂውን በመጠቀምም እስካሁን በአውስትራሊያ እና በደቡብ አፍሪካ ከ50 ሺህ በላይ ዛፎችን መትከል መቻሉንም ኩባያው አስታውቋል።
በዚህ የድሮን ቴክኖሎጂ በመጠቀምም እስከ ፈረንጆቹ 2024 ድረስ 100 ሚሊየን ዛፎችን ለመትከል እቅድ መያዙንም ነው ኤርሲድ ኩባንያ የገለፀው።