ፈረንሳይ የዩክሬንን ጦርነት መተንበይ አልቻሉም ያለቻቸውን የሀገሪቱ ወታደራዊ ስለላ ሃላፊ አባረረች
ፈረንሳይ ከነ አሜሪካ በተቃራኒ “ፑቲን በዩክሬን ላይ ጦርነት አይከፍቱም” የሚል አቋም ስታስተጋባ እንደነበር አይዘነጋም
የፈረንሳይ የስለላ ባለሙያዎች ግን “ችግሩ ወታደር ቤቱ ብቻ ሳይሆን እንደ ሀገር ያለው የስለላ መዋቅር ነው” እያሉ ነው
ፈረንሳይ የዩክሬንን ጦርነት መተንበይ አልቻሉም ያለቻቸውን የሀገሪቱን ወታደራዊ ስለላ ሃላፊ ጄኔራል ኤሪክ ቪዳውድን አባረረች፡፡
ጀኔራሉ ሃላፊነቱን ከተረከቡ ሰባት ወራት ቢሆናቸውም “ሁነቶች ተንትነው የማቅረብ ችሎታቸው” እና “ነገሮችን የመረዳት አቅማቸው” አናሳ መሆኑ ከሃላፊነታቸው ለመነሳት ምክንያት እንደሆነ ይነገራል፡
አሜሪካ ፑቲን በዩክሬን ላይ ወታደራዊ ዘመቻ ሊጀምሩ እንደሚችሉ ያላትን ስጋት በተደጋጋሚ ስትገልጽ የነበረ ሲሆን ፤ፈረንሳይ ግን በተቃራኒ “የለም! የማይመስል ነገር ነው” የሚል ድምዳሜ ስታስተጋባ እንደነበር የሚታወስ ነው፡፡
በሩሲያ በኩል ይደረግ የነበረውን ወታዳረዊ እንቅስቃሴ በቅርበት በመከታተልና ሊደረግ የሚገባው ዝግጅትን በተመለከተ ተንትኖ የማቅረብ ሃላፊነት ፤ የወታደራዊ ስለላ ሃላፊው ጄኔራል ኤሪክ ቪዳውድን እንደነበርም ነው እየተገለጸ ያለው፡፡
በዚህም የፈረንሳዩ ጦር ኃይሎች መሪ ጄኔራል ቲዬሪ ቡርክርድ ሃላፊነታቸው አልተወጡም ባሉዋቸውና የወታዳራዊ ስለላ ኃላፊ በሆኑት ጀኔራል ኤሪክ ቪዳውድን ላይ እርምጃ እንዲወስዱ መገደዳቸው የፈረንሳዩ የዜና ወኪል/ኤኤፍፒ/ ዘገባ ያመለክታል፡፡
ጄኔራል ቲዬሪ ቡርክርድ፤ የሀገራተቸው የስለላ መዋቅር እንቅስቃሴ የአሜሪካ እና የእንግሊዝ ያክል እንዳልሆነ ያላቸውን ሰጋት ባለፈው ወርሃ መጋቢት ገልጸው ነበር፡፡
"አሜሪካኖች ሩሲያውያን ጥቃት ሊሰነዝሩ ነው ብለው ነበር፣ ልክ ነበሩ" ሲሉም ነው የፈርነሳይ ጦር መሪ ከፈረንሳይ ወታደራዊ ስለላ መዋቅር ጋር በማነጻጸር የተናገሩት፡፡
ሩሲያ በዩክሬን ላይ ወታደራዊ ዘመቻ ከመጀመሯ በፊት ፕሬዚደንት ኢማኑኤል ማክሮን ከፑቲን ጋር ይገናኙ የነበረ ቢሆኑም፤ በፈረንሳይ በኩል ሁኔታውን ከመረዳትና ከመተንተን አንጻር ትልቅና አሳፋሪ ስህተት ተሰርቷል ሲሉም አክሏል ጀኔራሉ፡፡
ፈረንሳይ ላጋጠመው ውድቀት በወታደራዊ ስለላ ሃላፊው ላይ እርምጃ ብትወስድም ፤የስለላ ባለሙያው ፕሮፌሰር አሌክሳንደር ፓፓኤማኑኤል ግን ለውድቀቱ ወታደራዊ መዋቅሩ ላይ ብቻ ማነጣጠር ተገቢ አይደለም ሲሉ ተደምጧል፡፡
“ችግሩ እንደ ሀገር ያለው የስለላ መዋቅር ላይ ነው” ሲሉም ይሞግታሉ ፕሮፌሰሩ፡፡
ያም ሆነ ይህ ቀደም ባሉ ጊዜያት የፈረንሳይ የልዩ ሃይል አዛዥ በመሆን የገለገሉትና የአሁኑ የወታደራዊ ስለላ ሃላፊው ጄኔራል ቪዳውድ በሌሎች ምክንያቶችም ከፍተኛ ትችት እያስተናገዱ ያለ ይመስላል።
የውትድርና መረጃን በኃላፊነት ከያዙ ከሳምንታት በኋላ፣ አውስትራሊያ ከአሜሪካ እና እንግሊዝ ጋር የጸጥታ ስምምነት ለማድረግ ከፈረንሳይ ጋር የነበራትን ባለብዙ ቢሊዮን ዶላር የባህር ሰርጓጅ መርከቦችን ውል ስትሰርዝ የሳቸው ድክመት እንደነበረበት ይነሳል፡፡
በአውስትራሊያ፣ እንግሊዝ እና አሜሪካ መካከል የተደረሰው የአውኩስ ስምምነት በፈረንሣይ ውስጥ ከሰማያዊው መንገድ ወስጥ ከፍተኛ መደናገጥና ዲፕሎማሲያዊ አለመግባባት እንዲነሳ ምክንያት እንደነበር አይዘነጋም።