እየተካረረ በመጣው የዩክሬን ጉዳይ ላይ ለመምከር የፈረንሳይ መሪ ሩሲያ፤ የጀርመን ደግሞ አሜሪካ ናቸው
ሩሲያ ዩክሬንን ልትወር ነው በሚል በሞስኮ እና አሜሪካን ጨምሮ የኔቶ አባል በሆኑ ምዕራባዊ ሃገራት መካከል ከፍተኛ ውጥረት መንገሱ ይታወቃል
መሪዎቹ ውጥረቱን ለማርገብ በሚያስችሉ ዲፕሎማሲያዊ መፍትሔዎች ዙሪያ ይመክራሉ ተብሏል
እየተካረረ በመጣው የዩክሬን ጉዳይ ላይ ለመምከር የፈረንሳይ መሪ ሩሲያ፤ የጀርመን ደግሞ አሜሪካ ናቸው፡፡
ወደ ሞስኮ ያቀኑት የፈረንሳይ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ዛሬ ከሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ጋር ተገናኝተው እንደሚመክሩ ይጠበቃል፡፡
የጀርመኑ መራኄ መንግስት ኦላፍ ሹልዝ ደግሞ ወደ ዋሽንግተን አቅንተው ከፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ጋር ውጥረቱን ማርገብ በሚቻልባቸውዲፕሎማሲያዊ መንገዶች ዙሪያ ይመክራሉ ተብሏል፡፡
ሩሲያ ከዩክሬን ድንበር አቅራቢያ ጦሯን ማስጠጋቷን ተከትሎ ኪቭን ልትወር ነው የሚል እሰጣ ገባ መቀስቀሱ ይታወሳል፡፡
የሞስኮን አካሄድ የነቀፉ አሜሪካን ጨምሮ ሌሎች የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (ኔቶ) አባል ሃገራት ከድርጊቷ እንድትታቀብ በተደጋጋሚ አሳስበዋል፡፡
እጅግ ከባድ ዋጋ እንደሚያስከፍላት ሲያስጠነቅቁም ነበረ፡፡
ማስጠንቀቂያውን ችላ ብላ ወደ ድንበር የተጠጋውን ጦሯን የውጊያ ዝግጁነት የበለጠ እንዳደረጀች የሚነገርላት ሩሲያ በበኩሏ ኔቶ የሶቪዬት ህብረት አካል ወደነበሩ የምስራቅ አውሮፓ ሃገራት ማስፋፋቱን እንዲያቆም በማሳሰብ የደህንነት ዋስትና እንዲሰጣት ጠይቃለች፡፡
ይህም ሞስኮው ከዛሬ ነገ ኪቭን ትወራለች በሚል ስጋታቸውን በሚገልጹት በምዕራባውያኑ እና በሩሲያ መካከል ያለውን ውጥረት የበለጠ አባብሶታል፡፡
ከአሁን ቀደም ውጥረቱን በዲፕሎማሲያዊ መንገድ ለማርገብ የተደረጉ ጥረቶች እምብዛም ፍሬ አለማፍራታቸው ይታወቃል፡፡