ማክሮን እና ፑቲን በበይነ መረብ ተወያይተዋል
የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን በሩሲያ እና በዩክሬን ያለውን ወቅታዊ ውጥረት አስመልክቶ ወደ ሩሲያ እንደሚያቀኑ አስታወቁ፡፡
ፕሬዝዳንቱ ወደ ሞስኮ ጉብኝት የሚያደርጉት ከዓለም መሪዎች ጋር በስልክ ንግግር ካደረጉና መሻሻሎች ከመጡ እንደሆነም አንስተዋል፡፡ ኢማኑኤል ማክሮን ከሩሲያ እና ከዩክሬን አቻዎቻቸው ጋር ንግግር ማድረጋቸውን እንደሚቀጥሉ የገለጹ ሲሆን የትኛውንም አካል “አላገልም” ብለዋል፡፡
ፕሬዝዳንት ማክሮን ከሩሲያው አቻቸው ቭላድሚር ፑቲን ጋር በበይነ መረብ ውይይት ማድረጋቸውን ፍራንስ 24 ዘግቧል፡፡
የሁለቱ መሪዎች ውይይት በዩክሬንና በሩሲያ መካከል ያለውን ውጥረት እንዴት ማርገብ ይቻላል በሚለው ላይ ያተኮረ ነው፡፡
ማክሮን ከሩሲያው አቻቸው በተጨማሪ ከዩክሬን ፕሬዝዳንት ቮሎዶሚር ዜሌንስኪ ጋርም ተነጋግረዋል፡፡ በንግግሩ ሞስኮ የጸጥታ ዋስትና እንደምትፈልግ ከሩሲያ በኩል መነሳቱም ነው የተገለጸው፡፡
ከበይነ መረብ ውይይቱ በኋላ ማክሮን በቀጣይ ወደ ሞስኮ እንደሚያቀኑ የገለጹ ሲሆን ይህም በሩሲያ እና በዩክሬን ድንበር ያለውን ውጥረት በሰላም ለመፍታት ያለመ እንደሆነ ከፈረንሳይ ፕሬዝዳንት ጽ/ቤት የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡
የቱርኩ ፕሬዝዳንት ረሲፕ ጣይብ ኤርዶሃንም ዩክሬንን ጎብኝተዋል፡፡ በጉብኝቱ ሞስኮንና ኪቭን የተመለከተ ጉባዔ ለማዘጋጀት ጥያቄ አቅርበዋል ተብሏል፡፡ ቱርክን ጨምሮ ሌሎች ሀገራትም በጉዳዩ ላይ አስተያየቶችን እየሰጡ ናቸው፡፡
ሩሲያ እና ዩክሬን በሚዋሰኑበት ድንበር ላይ 100 ሺ የሩሲያ ወታደሮች መኖራቸውን አሜሪካ እና አጋሮቿ እየገለጹ ነው፡፡ ምዕራባውያን ሞስኮ፤ ኪቭን ለመውረር በዝግጅት ላይ እንደሆነች በተደጋጋሚ ቢከሷትም ፤ ሩሲያ ግን ይህን እያስተባበለች ነው፡፡