ፈረንሳይ ጦሯን ወደ ሳህል አካባቢ የላከችው ከዘጠኝ ዓመት በፊት በፍራንሷ ሆላንድ የፕሬዘዳንትነት ጊዜ ነበር
ፈረንሳይ ጦሯን ከዘጠኝ ዓመት በኋላ ከምዕራብ አፍሪካ አካባቢ ልታስወጣ መሆኗን ገልጸች፡፡
ፈረንሳይ በምዕራብ እና መካከለኛው አፍሪካ አገራት አክራሪ ጽንፈኞች የሽብር ድርጊቶችን እየፈጸሙ በመሆኑ እና ይሄንን ድርጊት ለማስቆም በሚል ነበር ወደ አካባቢው ጦሯን የላከችው፡፡ማሊ፣ቡርኪና ፋሶ፣ኒጀር እና ቻድ ደግሞ ከአምስት ሺህ በላይ የፈረንሳይ ጦር የሰፈረባቸው ሀገራት ናቸው፡፡
ይሁንና ፈረንሳይ ጦሯን ያስወጣችው በምን ምክንያት እንደሆነ በግልጽ አለመናገሯን ሲጂቲኤን አፍሪካ ዘግቧል፡፡
በማሊ በሶስት ካምፖች ሰፍሮ ያለው የፈረንሳይ ጦር አሁን ላይ ቱምቡክቱ ላይ ካለው ወታደራዊ ጣቢያ ውጪ ቀሪው ጓዙን በመጠቅለል ላይ ነው ተብሏል፡፡
የፈረንሳይ ፕሬዘዳንት ኢማኑኤል ማክሮን እስከ ቀጣዩ ሰኔ ወር ድረስ በምእራብ አፍሪካ አገራት ያለውን አብዛኛውን ጦር ወደ ፓሪስ የመመለስ እቅድ መያዙን ተናግረዋል፡፡
በሳህል አካባቢ ሰፍሮ የነበረው የፈረንሳይ ጦር አካባቢውን ለቆ ሲወጣ የአውሮፓ ህብረት አባል አገር ሌላ ጦር በአካባቢው ሊሰፍር እንደሚችልም ፕሬዘዳንት ማክሮን አክለዋል፡፡
የአውሮፓ አገራት ሰላም አስከባሪ ጦር ወደ ሳህል ቀጠና የሚሰማራው ከምዕራብ አፍሪካ አገራት ወደ አውሮፓ በመሻገር የሽብር ድርጊቶች እንዳይፈጸሙ ያለመ ነው ተብሏል፡፡
በፈረንሳይ ጦር የሳህል ኮማንድ አዛዥ ጀነራል ሎረንት ሚሾን በበኩላቸው ከ5 ሺህ በላይ ያለው የፈረንሳይ ጦርን ወደ 3 ሺህ ዝቅ የማድረግ እቅድ መያዙን ገልጸዋል፡፡
በፈረንጆቹ 2023 ዓመት ደግሞ በአካባቢው ያለውን የፈርንሳይ ጦር ቁጥርን በመቀነስ የምዕራብ አፍሪካ አገራት መንግስት በአሸባሪዎች ላይ ለሚወስዱት እርምጃዎች የአየር ጥቃቶችን ብቻ ወደ ማገዝ ይቀየራልም ብለዋል፡፡ፈረንሳይ ጦሯን ወደ ሳህል አካባቢ የላከችው ከዘጠኝ ዓመት በፊት በፍራንሷ ሆላንድ የፕሬዘዳንትነት ጊዜ ነበር፡፡
የማሊ እና ቡርኪናፋሶ ዜጎች በተለያዩ ከተሞች የፈርንሳይ ጦር አገራቸውን ለቀው እንዲወጡ የሚጠይቁ ሰላማዊ ሰልፎች መካሄዳቸው ይታወሳል፡፡