ሀገሪቱ አጫጭር በረራዎችን ለመሰረዝ የተገደደችው የአየር ብክለትን ለመከላከል በሚል ነው
ፈረንሳይ አጫጭር የሀገር ውስጥ በረራዎችን እንደምትሰርዝ ገለጸች፡፡
አውሮፓዊቷ ሀገር ፈረንሳይ በሀገር ውስጥ የሚደረጉ አጫጭር በረራዎች እንዳይደረጉ የሚከለክል ህግ በማውጣት ላይ እንደሆነች ገልጻለች፡፡
ፈረንሳይ በሀገሯ የሚደረጉ አጫጭር በረራዎችን መሰረዝ የሚያስችላትን ህግ ለማውጣት የተገደደችው በተለይም በግል ጄቶች የሚደረጉ በረራዎች አካባቢ አየርን እየበከሉ ነው በሚል ነው፡፡
በአውሮፓ የግል ጀቴች ብዛት ፈረንሳይ አንደኛዋ ሀገር ስትሆን እነዚህ ብዙ ቁጥር ያላቸው ቅንጡ ጄቶች የሚፈጁት ነዳጅ እና የሚለቁት በካይ አየር ከጥቅሙ ጉዳቱ አመዝኗል በሚል እንደሆነ ዩሮ ኒውስ ዘግቧል፡፡
ዋና መቀመጫውን ፈረንሳይ ፓሪስ ያደረገ አንድ የግል ጄት በሁለት ወር ውስጥ በአማካኝ 117 ሺህ ዮሮ ዋጋ ያለው የአውሮፕላን ነዳጅ እንደሚጠቀም የሀገሪቱ ትራንስፖርት ሚኒስትር አስታውቋል፡፡
የትራንስፖርት ሚኒስትሩ ክሌመንት ቦኔ እንዳሉት እነዚህ ቅንጡ የግል ጄቶች በሚለቁት በካይ ጋዝ በተጨማሪ በሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት ምክንያት የተፈጠረውን የነዳጅ እጥረት እንደሚያባብሰው ጠቁመዋል፡፡
የአውሮፓ ህብረት ኮሚሽን የፈረንሳይን ውሳኔ የደገፈ ሲሆን ከአውሮፓ ተቀራራቢ ከተሞች መካከል የሚደረጉ ቅርብ በረራዎችን እንደሚያግድም አስታውቋል፡፡
ፈረንሳይ በተለይም ከሁለት ሰዓት በታች የሚፈጁ በረራዎችን በሀገሯ እንዳይበሩ የሚከለክለውን ህግ በማጠናቀቅ ላይ መሆኗን የገለጸች ሲሆን የግል ጄቶች ደግሞ በረራውን ካደረጉ ከፍተኛ ግብር ልትጥል እንደምትችል ተገልጿል፡፡
ሀገሪቱ ተጓዦች ባቡር፣ ሳይክል እና ሌሎች ወደ ከባቢ አየር አነስተኛ በካይ ጋዝ የሚለቁ የትራንስፖርት አማራጮችን በማስፋፋት ላይ መሆኗንም አስታውቃለች፡፡