በፈረንሳይ ሰዎችን በጸጉራቸው ማሸማቀቅና መፈረጅ በህግ ማስጠየቅ ሊጀምር ነው
የሀገሪቱ ህግ አውጪዎች ከጸጉር ቀለም፣ ረዝመት እና አሰራር ጋር በተያያዘ የሚደረሱ በደሎችን የሚከላከል ህግ ለማጽደቅ እየመከረ ይገኛል

ረቂቅ ህጉ ጥፋተኞች እስከ 3 አመት እስራት እና 75 ሺህ ዩሮ ቅጣት ይተላለፍባቸዋል ይላል
ፈረንሳይ በአይነቱ ለየት ያለ ህግ ለማጽደቅ ፓርላማዋ በዛሬው እለት ይሰበሰባል።
አውሮፓዊቷ ሀገር ሰዎች በጸጉራቸው ምክንያት እንዳይፈረጁ፣ እንዳይሸማቀቁና በደል እንዳይደርስባቸው የሚከላከልና ጥፋተኞችን በወንጀል ተጠያቂ የሚያደርግ ህግ ላይ ትመክራለች።
“አፍሮ” የተሰኘው የጸጉር ቁርጥ ወይም አሰራር ከአፍሪካውያን ጋር ይገናኛል።
በተፈጥሮ ቁጥርጥር ወይም ፍሪዝ አይነት ጸጉር ያላቸውን ሰዎችም ከዚህ ዘር ይመዘዛሉ በሚል ሲፈረጁ ይታያል።
ሰዎችን በጸጉራቸው ቀለምና አሰራር፤ ርዝመት ስብእናቸው እንዲህ ነው የማለት መጥፎ ልማድ በፓሪስ ፈተና ከሆነ ሰነባብቷል።
በእኛም ሀገር ጸጉሩ በተፈጥሮውም ቁጥርጥር ቢሆን ከዱርየነት ጋር ሲያያዝ እናያለን።
በስራ ቦታም ሆነ በሌላ ስፍራ በጸጉራቸው ተፈጥሮ ምክንያት በርካታ ሰዎች የተለያዩ በደልና ተጽዕኖዎች ይደርስባቸዋል ያለችው ፓሪስ፥ በረቂቅ ህጉ ዙሪያ ዛሬ የህግ አውጪዎቿ ይከራከራሉ።
ረቂቁ ሰዎችን በጸጉራቸው ምክንያት ለማሸማቀቅ የሚሞክርና ሌላ በደል ለማድረስ የሞከረ አካል እስከ ሶስት አመት እስራትና እስከ 75 ሺህ ዩሮ ቅጣት ይተላለፍበታል ይላል ረቂቁ።
የፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ሬኔሳንስ ፓርቲ እና ቀኝ ዘመም ፓርቲዎች ረቂቁን መደገፋቸውን የሚያነሳው ፍራንስ 24 ፥ ህጉ ከጸደቀ ፈረንሳይ ከአሜሪካ ቀጥሎ ሁለተኛዋ ሀገር ትሆናለች ብሏል።
አሜሪካ በስራ ቦታ፣ በትምህርት ቤት እና በወታደራዊ ጣቢያ ከጸጉር ጋር የተገናኙ ማግለልና ተጽዕኖዎች እንዲቆሙ በሚል “ክራውን አክት” የተሰኘ ህግ አውጥታለች።
የሀገሪቱ 24 ግዛቶችም ህጉን ተግባራዊ እያደረጉት እንደሚገኙ ተገልጿል።