ሰሜን ኮሪያ በቻይና ስም ሰው ሰራሽ የጸጉር ምርቶችን ለዓለም ገበያ እያቀረበች ነው ተባለ
በምዕረቡ ዓለም ማዕቀብ የተጣለባት ሰሜን ኮሪያ በ2023 ከ167 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ማግኘቷ ተገልጿል
ሰሜን ኮሪያ በዓመት ከ1 ሺህ 600 ቶን በላይ ሰው ሰራሽ ጸጉር ለዓለም ገበያ አቅርባለች
ሰሜን ኮሪያ በቻይና ስም ሰው ሰራሽ የጸጉር ምርቶችን ለዓለም ገበያ እያቀረበች ነው ተባለ፡፡
የኑክሌር አረር እንዳትታጠቅ የተለያዩ የንግድ ማዕቀቦች የተጣሉባት ሰሜን ኮሪያ ባልታሰበ መልኩ የውጭ ምንዛሬ እያገኘች እንደሆነ ተደርሶበታል፡፡
ከፈረንጆቹ 2006 ጀምሮ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት፣ በአሜሪካ እና አውሮፓ ህብረት የንግድ ማዕቀብ የተጣለባት ሰሜን ኮሪያ ሰው ሰራሽ ጸጉር ወይም ዊግ ምርቶችን በቻይና የተሰራ በማለት ለዓለም ገበያ እያቀረበች ነው ተብሏል፡፡
ሀገሪቱ በተጠናቀቀው 2023 ዓመት ብቻ ከ1 ሺህ 600 ቶን በላይ ሰው ሰራሽ ጸጉር፣ ጺም እና ሌሎች የመዋቢያ ምርቶችን በመላክ 167 ሚሊዮን ዶላር ገቢ እንዳገኘች ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
ሰሜን ኮሪያ ይህን ያልታሰበ ምርት ለምንግዜም ተቀናቃኟ ደቡብ ኮሪያ ሳይቀር በእጅ አዙር ስትሸጥ ነበር የተባለ ሲሆን አሜሪካ፣ አውሮፓ እና ጃፓን ዋነኛ የምርቶቿ መዳረሻ ሆነዋል ተብሏል፡፡
የሀገሪቱ ነጋዴዎች በሰሜን ኮሪያ የተመረቱ ሰው ሰራሽ ጸጉር ወደ ቻይና በማጓጓዝ በቻይና የተሰራ የሚል ስም እየጨመሩ ያለምንም እንከን ከፍተኛ ገቢ ሲያገኙ እንደቆዩ በዘገባው ላይ ተጠቅሷል፡፡
ሰሜን ኮሪያ የድንጋይ ከሰል፣ ነዳጅ እና ሌሎች ማዕድናት በስፋት ያላት ሀገር ብትሆንም በተጣለባት ማዕቀብ ምክንያት ሀብቷን ለዓለም ገበያ ማቅረብ አልቻለችም፡፡
ቻይና እና ሩሲያ ዋነኛ የንግድ አጋሯ ሲሆኑ ከተመድ ውጪ እንደ አሜሪካ ያሉ የተናጠል ማዕቀቦችን የማክበር ግዴታ የለብንም በሚል ንግዳቸውን እንደቀጠሉ ናቸው፡፡
ተመድ በሰሜን ኮሪያ ላይ የንግድ ማዕቀብ የጣለ ቢሆንም ማዕቀቡ የሚመለከታቸው የትኞቹን የምርት አይነቶች እንደሆነ በግልጽ አለማስቀመጡ ለትግበራው አመቺ አልሆነም ተብሏል፡፡
ፒዮንግያግ ሰው ሰራሽ ጸጉር እየላከች የምታገኘው ገቢ ለማስቀረት እነ አሜሪካ መታወቁን ተከትሎ አዲስ ማዕቀብ ሊጣሉባት ይችላል የሚል ስጋት ተነስቷል፡፡