ፓሪስ ውጥረት ለበዛበት የፈረንሳይና እስራኤል የኔሽንስ ሊግ ጨዋታ 6 ሺህ 500 ፖሊሶች አሰማራች
በአምስተርዳም የተከሰተው ግጭት እንዳይደገም በስታድ ደ ፍራንስ ስታዲየም የሚገቡ ተመልካቾች ቁጥር እንዲቀንስ ተደርጓል
እስራኤል የዛሬውን ጨዋታ ለመመልከት ወደ ፓሪስ የሚያቀኑት ደጋፊዎች ከ100 እንዳይበልጡ አድርጋለች
ፓሪስ የዛሬ ምሽቱ የፈረንሳይ እና እስራኤል የአውሮፓ ኔሽንስ ሊግ ጨዋታ በሰላም እንዲጠናቀቅ በሺዎች የሚቆጠሩ የጸጥታ ሃይሎችን ማሰማራቷን አስታወቀች።
ባለፈው ሳምንት በአምስተርዳም ከአያክስ ጋር የዩሮፓ ሊግ ጨዋታውን ያደረገው የእስራኤሉ ማካቢ ቴል አቪቭ ደጋፊዎች ላይ የደረሰውን ጥቃት ተከትሎ የዛሬው የፓሪስ ጨዋታ ውጥረት በዝቶበታል።
የፓሪስ ከተማ ፖሊስ አዛዥ ላውረንት ኑኔዝ እንዳስታወቁት 4 ሺህ ፖሊሶች ከተማዋን ሲቃኙ ይውላሉ፤ 2 ሺህ 500 የሚሆኑት ደግሞ በስታድ ደ ፍራንስ ስታዲየምና በህዝብ ትራንስፖርት መስጫዎች ይሰማራሉ።
1 ሺህ 600 የግል የደህንነት ባለሙያዎች እና የጸረ ሽብር ፖሊስ አባላት ደግሞ በስታዲየሙ ውስጥ የእስራኤል ተጫዋቾች እና ደጋፊዎችን በንቃት ይጠብቃሉ ነው ያሉት ኑኔዝ።
“ጨዋታው በጂኦፖለቲካዊ ውጥረት ምክንያት ከፍተኛ አደጋ ተደቅኖበታል፤ ይሁን እንጂ ማንኛውንም የጸጥታ ሁኔታውን የሚረብሽ ተግባር አንፈቅድም” በማለትም ፓሪስ የአምስተርዳሙ ክስተት እንዳይደገም ዝግጁ መሆኗን ተናግረዋል።
80 ሺህ ተመልካቾችን መያዝ የሚችለው ስታድ ደ ፍራንስ ስታዲየም ዛሬ 20 ሺህ ብቻ ተመልካቾችን ያስተናግዳል ተብሏል።
በእስራኤል መንግስት ምክር መሰረት ጨዋታውን ለመመልከት ወደ ፓሪስ የሚያቀኑ ደጋፊዎች ቁጥር ከ100 እንዳይበልጥ መደረጉን ቢቢሲ ዘግቧል።
ፈረንሳይ፣ ቤልጂየም እና ኔዘርላንድስ የዘር ግንዳቸው ከሰሜን አፍሪካ የሆኑ በርካታ ሙስሊም ነዋሪዎች አሏቸው። በሀገራቱ የሚገኙ አይሁዳውያን ከሙስሊሞቹ አንጻር ዝቅተኛ ነው።
የማካቢ ቴል አቪቭ ደጋፊዎች ባለፈው ሳምንት በኔዘርላንድስ አምስተርዳም ጥቃት እንዲፈጸምባቸው የሚገፋፉ ድርጊቶችን መፈጸማቸው መዘገቡ ይታወሳል።
ደጋፊዎቹ ጸረ አረብ መፈክሮችን ማሰማታቸው፣ የፍልስጤም ሰንደቅ አላማን ከተሰቀለበት ቀደው ማውረዳቸው፣ በዝርፊያ እና በታክሲ ጥቃት ላይ መሳተፋቸውን ተከትሎ ድብደባ እንደተፈጸመባቸው የአምስተርዳም ፖሊስ ባወጣው ሪፖርት ማመላከቱም አይዘነጋም።
የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን በአውሮፓ ለሚገኙ አይሁዳውያን አጋርነቴን ለማሳየት የዛሬውን ጨዋታ በስታድ ደ ፍራንስ በመገኘት እመለከታለሁ ብለዋል።
የቀድሞው የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ሚሸል ባርኔር እና የቀድሞ ፕሬዝዳንቶች ፍራንሿ ኦላንድ እና ኒኮላስ ሳርኮዜም በስታዲየም ይገኛሉ ተብሏል።
የፍልስጤም ደጋፊዎች በፓሪስ በዛሬው እለት ለማካሄድ ያሰቡት የተቃውሞ ሰልፍ ውጥረቱን እንዳያባብሰው ተሰግቷል።
የእስራኤልና ፈረንሳይ መሪዎች ግንኙነት ባለፉት ሳምንታት ይበልጥ ሻክሯል። በተለይ ፕሬዝዳንት ማክሮን የእስራኤሉን ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ በጋዛ እና ሊባኖስ “አረመኔያዊ ድርጊት እያስፋፋ ነው” ማለታቸው የፈረንሳይ አይሁዶችን ጭምር አስቆጥቷል።
ማክሮን “ኔታንያሁ የመንግስታቱ ድርጅት የተኩስ አቁም ሃሳብ መቀበል አለበት፤ ምክንያቱም እስራኤልም በተመድ ውሳኔ ነው የተመሰረተችው” በሚል የሰጡት ሃሳብም በእስራኤል እንደ ስድብ ተቆጥሯል።
እስራኤል በምላሹ በምስራቅ እየሩሳሌም በሚገኝ የፈረንሳይ ቤተክርስቲያን ውስጥ ሁለት የጸጥታ ሃይሎችን በቁጥጥር ማዋሏ ፓሪስን ማስቆጣቱ አይዘነጋም።