የራፋህ ነዋሪዎችን በሃይል ማፈናቀል ከጦር ወንጀል ይቆጠራል - ማክሮን
የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ከኔታንያሁ ጋር በስልክ ባደረጉት ውይይት እስራኤል በዌስትባንክ ከ800 ሄክታር በላይ መሬት በወረራ መያዟንም ተቃውመዋል
ፓሪስ በጋዛ ፈጣን እና የመጨረሻ የተኩስ አቁም ረቂቅ የውሳኔ ሃሳብ ለጸጥታው ምክርቤት እንደምታቀርብ ፕሬዝዳንት ማክሮን ተናግረዋል
እስራኤል ጦርነትን ሸሽተው በራፋህ የተጠለሉ ፍልስጤማውያንን በሃይል ማስወጣት ከጦር ወንጀል የሚቆጠር ነው አሉ የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን።
ፕሬዝዳንቱ ከእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ጋር በስልክ ተወያይተዋል።
እስራኤል በትናንትናው እለት በሃይል በያዘችው ዌስትባንክ ከ800 ሄክታር በላይ መሬት መከለሏን ማስታወቋ ይታወሳል።
“የመንግስት ይዞታ” ነው የተባለው የፍልስጤማውያን መሬት የሰፈራ ቤቶችና የንግድ ህንጻዎች እንደሚገነቡበትም ተገልጿል።
ማክሮን ከኔታንያሁ ጋር በስልክ ሲወያዩ ይህን የቴል አቪቭ ውሳኔ “አጥብቀው አውግዘውታል” ብሏል የፕሬዝዳንቱ ጽህፈት ቤት ባወጣው መግለጫ።
በጋዛው ጦርነት ዙሪያ እስራኤልን በተደጋጋሚ የወቀሱት ማክሮን በራፋህ ሊጀመር የታሰበው ጦርነት ከፍተኛ ቀውስ እንደሚያስከትል ለኔታንያሁ ነግረዋቸዋል ይላል መግለጫው።
እስራኤል የተዘጉ የሰብአዊ ድጋፍ ማስተላለፊያዎች እንድትከፍትም ጠይቀዋል።
ፓሪስ በጋዛ አስቸኳይና የማያዳግም የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረስ እንደምትፈልግና በጸጥታው ምክርቤት ረቂቅ የውሳኔ ሃሳብ እንደምታቀርብም ነው ፕሬዝዳንቱ ያነሱት።
ማክሮን ከዮርዳኖሱ ንጉስ አብዱላህ ጋርም በጋዛ በረሃብ ለሚገኙ ፍልስጤማውያን በፍጥነት መድረስ ስለሚቻልበት ሁኔታ መወያየታቸውን አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ዘግቧል።
ፓሪስ እና አማን በጋዛ ከአውሮፕላኖች ላይ ድጋፎችን በማድረስ ላይ መሆናቸው ይታወቃል።
የሀገራቱ መሪዎች በውይይታቸው ንጹሃንን ለረሃብ ማጋለጥ ተቀባይነት “ምንም አይነት አመክንዮ የሌለው” ነው፤ በዚህ ላይ የራፋህ ጦርነት ከተጀመረ ቀውሱ ይበልጥ አስፈሪ ይሆናል ማለታቸውንም ተዘግቧል።
እስራኤል በራፋህ የእግረኛ ጦሯን በማስገባት ጦርነት ለመጀመር መዘጋጀቷን ማሳወቋ አለማቀፍ ተቃውሞ ቢያስነሳም በቅርቡ የጦርነቱን እቅድ አጽድቃ የንጹሃንን ህይወት አደጋ ላይ የሚጥለው ጦርነት አይቀሬ መሆኑን አረጋግጣለች።